ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች የማይበገር አህጉራዊ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች የማይበገር አህጉራዊ የጤና ሥርዓት ለመገንባት ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ  ገለጹ፡፡ 

"የአፍሪካ የጤና ባለሙያዎችን አቅም ለመጪው ዘመን ማዘጋጀት፦ ትብብርን፣ ቴክኖሎጂን፣ ፈጠራንና አመራርን መጠቀም" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት ጉባኤ ተጠናቋል።


 

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያላትን ልምድ እና የካበተ አቅም በመጠቀም የጎረቤት ሀገራት ተማሪዎችን በነጻ በማስተማርና በጤና አገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ያላትን ልምድ ለጉባኤው አካፍላለች።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ጉባዔው በአህጉሪቱ ለሚያጋጥሙ የጤና ተግዳሮቶች በአፍሪካውያን የሚመራ መፍትሄ ማስቀመጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

በጉባኤው ላይ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የሕክምና ሳይንስ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በጋራ አህጉራዊ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል።

በአህጉሪቱ የሚገኙ የሕክምና ማሰልጠኛ ተቋማት ዘመኑ ከዋጀው የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር እንዲራመዱ እና ብቁ የሰው ኃይል እንዲያፈሩ ለማስቻል ምክክር መደረጉንም አንስተዋል።

በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ የወደፊቱን የጤና ሥርዓት ተግዳሮቶች በብቃት መቋቋም የሚያስችል ጠንካራና ተለዋዋጭ አቅም ለመገንባት የሚያስችል የጋራ አቋም መያዙን አስታውቀዋል። 

በተጨማሪም የአፍሪካን የጤና ሥርዓት ለማጠናከርና የሥልጠና ጥራትን ለማሻሻል ሰፊ ምክክር ተደርጓል።

በዚህም ኢትዮጵያ ለጤናው ዘርፍ የሰው ኃይል ግንባታ የሰጠችውን ልዩ ትኩረት፣ የጎረቤት አገራት ተማሪዎችን በነጻ በማስተማርና የሕክምና መሠረተ ልማት ማስፋፋት ረገድ ያላትን ልምድ በማካፈል አርዓያነት ያለው ተግባር ማከናወኗን ገልጸዋል።

በቀጣይም በጉባኤው የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት፣ ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር እንደምትሠራ ተናግረዋል።


 

የአፍሪካ የሕክምና ትምህርት ቤቶች ስብስብ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ላዮኔል ግሪን ቶምሰን በበኩላቸው፤ በጉባኤው የተቀመጡ አቅጣጫዎች የአህጉሪቱን የጋራ አቅም በማቀናጀት አፍሪካን ከውጭ የሕክምና ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ተላቃ ራሷን እንድትችል ለማድረግ ወሳኝ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም