የኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የሀገርን ገጽታ የቀየሩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የሀገርን ገጽታ የቀየሩ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):-የኮሪደር ልማትና ሌሎች ፕሮጀክቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የሀገርን ገጽታ የቀየሩ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ የሥራ ዘመን 3ኛ ዓመት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ዋና ዓላማ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ማነቃቃት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ልማቱ ከከተሞች ደረጃና ውበት፣ ከመሠረተ ልማት ትስስር፣ ከደህንነት እንዲሁም ከመብራት አገልግሎትና ከሌሎች ተያያዥ ጠቀሜታዎች አንጻር ያለውን ፋይዳም አብራርተዋል።
የኮሪደር ልማትና ሌሎች ስትራቴጂያዊ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ገጽታ የሚቀይሩ በመሆናቸው፤ መላው ሕዝብ፣ ባለሀብቶችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሀገር ግንባታው በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወቃል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በተከናወኑ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት ከፍ ወዳለ ደረጃ እያሸጋገሩት እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የልማት ሥራዎቹ ለትውልዱ ትምህርት የሚሰጡና የሥራ ባህልን ለማሳደግ ምሳሌ የሚሆኑ ያሉት ነዋሪዎቹ፥ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርን ገጽታ መቀየራቸውን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ተሊሌ ኃብተማርያም ፤ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የልማት ሥራዎች ወጣቶችና ሴቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
አቶ ሙደስር ኡመር በበኩላቸው፤ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ በተከናወኑ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ከተሞችን ንጹሕና ለነዋሪዎች ምቹ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ትውልዱ ከዚህ ትምህርት ሊወስድ፣ በሚከናወኑ ሥራዎች በትጋት ሊሠራና ከመንግሥት ጎን በመሆን ለሀገር ግንባታ አሻራውን ሊያሳርፍ ይገባልም ብለዋል።
ሌላዋ የመዲናዋ ነዋሪ ወይዘሮ አዲስ ዓለም ምስግና በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ዕቅዶችን ማሳካት እንደሚቻል በተጨባጭ ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።
የልማት ሥራዎቹ በስራ እድል ፈጠራና የኑሮ ደረጃን በማሻሻል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት አሳድገዋል ያሉት አቶ ታምራት ቶሎሳ፥ ከኢትዮጵያ ባለፈ አፍሪካውያንን ለላቀ ልማት ያነሳሱ ናቸው ብለዋል።