ቀጥታ፡

ዋናው የምክክር ጉባኤ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሰረት የሚጥል ነው - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):-ዋናው የምክክር ጉባኤ መሠረታዊ ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታትና መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሰረት የሚጥል መሆኑን በጉባኤው የሚሳተፉ ተመካካሪዎች ገለጹ።

ከሐምሌ 8 ጀምሮ 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተመካካሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ስታከናውነው የቆየችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት አሁን ላይ የመጨረሻና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ ምክክር የሚካሄድባቸው ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች የተለዩ ሲሆን በእነዚህም ላይ በዝርዝር ለመምከርና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማስቀመጥ፣ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ የተወከሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች ወደ አዲስ አበባ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና ዳያስፖራ አስተባባሪ አቶ ረታ ጌራ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፥ ከክልሎች እንዲሁም ከዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚመጡ ተመካካሪዎች ለዋናው የምክክር ጉባኤ አዲስ አበባ እየገቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ለተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎችም በተዘጋጁ ምቹ ቦታዎች ላይ አቀባበል እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች በበኩላቸው፣ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ ለመመካከር ዕድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።


 

ከተመካካሪዎቹ መካከል ከፌደራል ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ወገን የመጡት ሀንፍሬ ከዳፎ፣ ይህ ታሪካዊ መድረክ በአለመግባባቶች ላይ በመመካከር ጠንካራ አንድነት ያላትና የተረጋጋች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የማህበረሰብ መሪዎች መካከል የመጡት ዘርፌ በቀለ በበኩላቸው፣ በዚህ ወሳኝ ወቅት ተመካክረን፣ ተደማምጠን እና ተቀራርበን ጠንካራ ሀገር ለሚመጣው ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ተስፋ ሰንቀናል ብለዋል።


 

ከአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን የወጣት ተወካይ ያረጋል ታደሰ፥ የምክክር ጉባኤው ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

ምክክሩ ለዘላቂ ሀገራዊ እና ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ያሉት ደግሞ ከጋምቤላ ክልል የመጡት ተመካካሪ ሉክ ኬዌ ናቸው።

ከደቡብ ኢትዮጵያ የመጡት ተመካካሪ ኢንጂነር ምንትዋብ ምንጃር እና ከአዲስ አበባ የመጡት ገረመው ጫልቃ መድረኩ ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በነጻነት በማንሸራሸር ለቀጣይ ትውልድ የምትሆን ጠንካራ ሀገር የሚገነቡበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም