ቀጥታ፡

የብሔራዊ ፓርኮችን ደህንነት ለመጠበቅ በተሰሩ ስራዎች ውጤት እየተገኘ ነው

አርባ ምንጭ ፤ሐምሌ 1/2018 (ኢዜአ)፡- የብሔራዊ ፓርኮችን ደህንነት ለመጠበቅ በተሰሩ ስራዎች ውጤት እየተገኘ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የብሔራዊ ፓርኮችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት እና በተገኙ ውጤቶች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ ስለሺ ግርማ፤ ብሔራዊ ፓርኮች የብርቅዬ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት መገኛ ናቸው ብለዋል።

የቱሪዝም ልማት በአንድ አካል ብቻ ጥረት የሚረጋገጥ ባለመሆኑ መንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑና ከልማት አጋሮች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ሰሜንና ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች የተከናወኑ ተግባራት ለዘርፉ ልማት ሰፊ ልምድ የተገኘበት በመሆኑ በዚህ ሥራ የተገኘውን ውጤት የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ አካል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደተናገሩት ብሔራዊ ፓርኮችን ከሰው ሰራሽ ችግሮች ለመታደግ የተቀናጁ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።


 

ከዚህ ቀደም ሰሜንና ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች ለልቅ ግጦሽ፣ ለእርሻና ለሰፈራ እንዲሁም ለእሳት አደጋና ለሕገ-ወጥ አደን የተጋለጡ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ችግሮቹን ከመሠረቱ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግሥት ከጀርመን ልማት ባንክ ጋር በመተባበር ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ባከናወናቸው ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በተለይ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ በመቻሉ የወሰንና የእሳት አደጋ ችግሮች፣ የልቅ ግጦሽ፣ የእርሻ፣ የሰፈራና ሕገ-ወጥ አደን ችግሮች እየተቀረፉ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይ በሰሜን ተራሮችና በባሌ ብሔራዊ ፓርኮች ጥበቃ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ወደ ሌሎች ፓርኮች ለማስፋፋት መታቀዱን ጠቁመዋል።

መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ ሲሆን የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ባለሥልጣን፣ የብሔራዊ ፓርኮች ኃላፊዎች፣ የክልሎች ዱር እንስሳት ጥበቃ የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም