ቀጥታ፡

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመር፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ለተያያዙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ ነው

ጅማ ፤ሐምሌ 1/2018(ኢዜአ)፡- የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመር፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ለተያያዙ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ ነው ሲሉ የጅማ ዞን ማና ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በጅማ ዞን ማና ወረዳ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የዞኑና የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።


 

የማና ወረዳ ነዋሪዎች መንግሥት ለማኅበረሰቡ ጥያቄዎች ቅድሚያ በመስጠት እንደ መሶብ ያሉ ማዕከላትን ወደ ሥራ ማስገባቱ የገባውን ቃል በተግባር እየፈጸመ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማሩት የወረዳው ነዋሪ አቶ ዛኪር አወል በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም ለአንድ ጉዳይ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ይባክንባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ዛሬ አገልግሎት የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይህንን እንግልት እንደሚያስቀርላቸው ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው ነዋሪ አቶ መሐመድኑር ሸምሱ በበኩላቸው፣ ለዘመናት ይመኙት የነበረውን ፈጣን አገልግሎት በማዕከሉ ማግኘት መጀመራቸውን ጠቅሰው፣ አገልግሎቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ የተቀላጠፈ እንዲሁም ጊዜና ገንዘብን የሚቆጥብ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ የማዕከሉ ስራ መጀመር ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያገኙ ተስፋ እንዲሰንቁ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።


 

የማና ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሰመሩዲን አህመድ በበኩላቸው፣ በወረዳው በበጀት ዓመቱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 32 ፕሮጀክቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

ከተገነቡት መሠረተ ልማቶች መካከል ሁለት ድልድዮች፣ የወጣቶች መሥሪያ ሼዶች፣ የአስተዳደር ሕንጻ እንዲሁም የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በማዕከሉ 88 ዓይነት አገልግሎቶች በ9 መስኮቶች እንደሚሰጡ የገለጹት አስተዳዳሪው፣ በወረዳው ከሚገኙ 14 ሴክተሮች ውስጥ 10 የሚሆኑት ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ መደረጉ የተገልጋዩን እርካታ ከፍ እንዳደረገው አብራርተዋል።

በዛሬው ዕለት በወረዳው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የ362 አቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታና እድሳት መጀመሩን አንስተዋል።


 

የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቲጃኒ ናስር፣ በዞኑ በማኅበረሰቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የሚመልሱ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለነዋሪዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ የመንግሥትንና የዜጎችን ከአላስፈላጊ ወጪ መታደጉን ጠቁመዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ቀላልና ዲጂታላይዝ በማድረግ የተገልጋዩን እርካታ የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ቲጃኒ አክለዋል።

ከመሠረተ ልማት ግንባታዎች በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የበርካታ አቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም