ቀጥታ፡

መንግስት ለቅድመ መደበኛ ትምህርት የሰጠው ትኩረት ለትውልድና ለሀገር ግንባታ ትልቅ መሠረት የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- መንግስት የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን ከመሰረቱ ለማነጽ በቅድመ-መደበኛ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን ታላቅ መሰረት መሆናቸውን የኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትምህርት ዘርፍን በተመለከተ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ 35 ሺህ የሚሆኑ መዋለ ሕፃናት መገንባታቸውን ጠቁመው ይህ የመዋለ ሕፃናት ግንባታ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑንና ይህም የትምህርት መሠረትን ከታች ጀምሮ ለማጠንከር ታስቦ የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢዜአ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ተከትሎ ያነጋገራቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳመለከቱት፤ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑንና ማብራሪያውንም በቅርበት መከታተላቸውን ገልጸዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይም በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ለመዋዕለ ሕፃናት የተሰጠው ትኩረት ለነገዋ ታላቅ ኢትዮጵያ ጠንካራ መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል መጋቢ ስርዓት አበራ ግሩም እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በአገር ደረጃ ለትምህርት ሥርዓቱና ለጥራቱ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ እንዲሁም ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ አገሩን የሚወድና ኃላፊነቱን የሚወጣ ትውልድ ለመፍጠር በትምህርት ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት 35 ሺህ የሚሆኑ መዋዕለ ሕፃናት መገንባቸው ሕፃናት መልካም መሠረት ኖሯቸው እንዲያድጉ የሚያስችልና የነቃና የበቃ ትውልድ ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ዮሐንስ ይገዙ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ለትምህርት ጥራት የተሰጠው ትኩረት የተማረና ምክንያታዊ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ በተከናወነው ሥራ በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሰፊ ዕድል መፈጠሩን አንስተው፣ በቀጣይም የተገኘውን ውጤት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።

አቶ ተሾመ ኤርጎ በሰጡት አስተያየትም፤ የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችን በቀጥታ ከማሻሻል ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በመሆኑም መንግሥት በዚህ ረገድ የጀመረው ውጤታማ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

መንግሥት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩና ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል እንዲችሉ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ወርቅነሽ ማሞ ናቸው።


 

ለዚህም የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን ለአብነት መጥቀስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም