ቀጥታ፡

መንግሥት ባለፉት ዓመታት የተከተለው የዲፕሎማሲ መርህ የኢትዮጵያን ተሰሚነት ያሳደገና የውሳኔ ሉዓላዊነቷን ያስከበረ ነው - የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):-መንግሥት ባለፉት ዓመታት የተከተለው ብሔራዊ ጥቅምን ያማከለና ገቢር ነበብ የዲፕሎማሲ መርህ የኢትዮጵያን ተሰሚነት ያሳደገና የውሳኔ ሉዓላዊነቷን ያስከበረ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዲፕሎማሲው ዘርፍና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ በመቋቋም፣ በመጠቀምና መግራት የዲፕሎማሲ መርህ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ አቅም ገንብታለች ብለዋል።

ውስብስብ፣ ተለዋዋጭና ኢ-ተገማች በሆነ አውድ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅምን ያማከለና ገቢር ነበብ የዲፕሎማሲ አካሄድ መከተል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የመንግሥት መርህ የኢትዮጵያን የውሳኔ ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም ውሳኔዎች ውስጥ ሌሎች አካላት ተፅዕኖ እንዲያደርጉ አለመፍቀድ ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ ስኬቶች አስመዝግባለች።

ኢትዮጵያ  የባህር በር ጥያቄን ያነሳችበትና በዓለም አቀፍ መድረክ ተቀባይነት ያገኘችበት ወቅት መሆኑም የመንግሥትን ገቢር ነበብ የዲፕሎማሲ አካሄድ ውጤታማነት ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር መሆኗ ባለፉት አምስት ዓመታት ከተመዘገቡ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ስኬቶች አንዱ ነው ብለዋል።

መንግሥት ባለፉት አምሥት ዓመታት የተከተለው በሳል የዲፕሎማሲ መርህ ኢትዮጵያን ከዳር ተመልካችነት ወደ ተደማጭነትና የዓለም አቀፍ ጥምረቶች ንቁ ተሳታፊ ወደመሆን እንዳሸጋገራት ተናግረዋል።

የሀገራችንን የባህር በር ጥያቄ ተገቢነትን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ መደረጉም የስኬታማ የዲፕሎማሲያዊ ስራ ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች መካሄዳቸው እና ኢትዮጵያ ታላቅ የአየር ንብረት ጉባዔን ለማስተናገድ መመረጧ የዲፕሎማሲ ተሰሚነቷ እያደገ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ በመስጠት የተከተለችው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውጤታማ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል አቡኔ ዓለም ናቸው።

በተለይም የሀገር ውስጥ የልማት ስራዎች ለዲፕሎማሲው ስኬት መሰረት መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ማህበረሰብና መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የተመለከቷቸው እንደ አረንጓዴ ዐሻራና የኮሪደር ልማት ያሉ ሥራዎች የሀገርን ገጽታ የለወጡና ተሰሚነቷን ያሳደጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም