በክልሉ የገቢ አቅምን በማሳደግ ሁለንተናዊ ልማትን ለማፋጠን የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የገቢ አቅምን በማሳደግ ሁለንተናዊ ልማትን ለማፋጠን የተጀመሩ ሥራዎች ይጠናከራሉ
ወላይታ ሶዶ፤ ሐምሌ 1/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የገቢ አቅምን በማሳደግ የክልሉን ሁለተናዊ ልማት ለማፋጠን የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ አስተዳደር አስታወቀ።
በወላይታ ሶዶ ከተማ የ2019 በጀት ዓመት የደረጃ "ለ" ግብር አሰባሰብ እና የንግድ ፈቃድ እድሳት ማስጀመሪያ ንቅናቄ ተካሂዷል።
በንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ ዘርፍ አማካሪ አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ እንዳሉት ግብር ለክልሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጾ አለው።
ክልሉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ከእርዳታ ጥገኝነት ከማላቀቅ ባለፈ የክልሉን ልማት በማፋጠን የህዝብን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል።
በመሆኑም የክልሉን የገቢ አቅም በማሳደግ የክልሉን ሁለተናዊ ልማት ለማፋጠን የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ሁሉም ግብር ከፋይ ግብሩን በአግባቡና ታማኝነት ሲከፍል በገበያው ውስጥ ፍትሃዊና ጤናማ ውድድር ይፈጠራል ያሉት አማካሪው፣ ህገ ወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን በቅንጅት ለመከላከል ይሰራል ብለዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማሪያም በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የከተማዋን እድገት ለማስቀጠል የውስጥ ገቢን አሟጥጦ ለመሰብሰብ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የግብር ከፋዮን እንግልት ለማስቀረት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው የሚሰሩ አምስት የግብር መክፈያ ማዕላትን ወደ ሥራ ለማስገባት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
በግብር ዓመቱ በከተማው ካሉ ከ13 ሺህ 790 በላይ የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን የተናገሩት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አማረች ዮሐንስ ናቸው።
ሁሉም የግብር መክፈያ ማዕከላት የቴሌ ብር ሲስተምን ጨምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከእጅ ንኪኪ ነፃ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡ ሙሉ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ትግበራ መገባቱንም ጠቁመዋል።
ግብራቸውን በቴክኖሎጂ ታግዘው መክፈላቸው የጊዜና የጉልበት ብክነት እንዳስቀረላቸው የገለጹት ደግሞ አቶ አብርሃም ክፍሌ እና ወይዘሮ ትዝታ ደርጌ የተባሉ የከተማዋ ግብር ከፋዮች ናቸው።
ቀድመው መክፈላቸው በኋላ ይገጥማቸው ከነበረ የጊዜ ጥበት እንደሚታደጋቸው ገልጸው፣ ሌሎች ግብር ከፋዮችም ግብራቸውን በታማኝነት ቀድመው በመክፈል ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት በተካሄደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት እንደሀገር በትሪሊዮን የሚቆጠር ገቢ እንደተገኘ መግለጻቸው ይታወሳል።
በግብር ዓመቱ ዲጂታል አሰራር መተግበሩና መደበኛ ካልሆኑ 43ሺህ የንግድ እንቅስቃሴዎች ግብር እንዲሰበሰብ መደረጉ ዘንድሮ የተገኘውን ገቢ ማሳደጉንም አመልክተዋል።
ክልሎችም በቀጣይ የገቢ አቅማቸውን በማጠናከር ራሳቸውን ከመቻል ባለፈ የሚመደብ በጀትን ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንዳለባቸው ማስገንዘባቸው የሚታወስ ነው።