ኢትዮጵያውያን በምርጫው ያሳዩት የጋራ አቋም የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት ከሀገር በታች መሆኑን ያስገነዘበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በምርጫው ያሳዩት የጋራ አቋም የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት ከሀገር በታች መሆኑን ያስገነዘበ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 1/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያን በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያሳዩት የጋራ አቋም የትኛውም የፖለቲካ ልዩነት ከሀገር በታች መሆኑን እንዳስገነዘበ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀመንበርና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን አለምነህ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች የፅንፈኞች ማስፈራሪያና ዛቻ ሳይበግራቸው ከማለዳ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ድምፅ በመስጠት፣የካበተ ዕሴታቸውን በተግባር ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምፅ "ፅንፈኝነትን፣ ባንዳነትንና ዘረኝነትን በመፀየፍ የጋራ ሀገርን ማልማትና ማበልፀግ እንፈልጋለን" የሚል ጉልህ መልዕክት ለዓለም ማስተጋባት እንደቻሉ አስገንዝበዋል።
የባንዳነትና የፅንፈኝነት ፍላጎትን ማሸነፍ የሚቻለው ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን በስልጡን ሀገራዊ ውይይት መፍትሔ መስጠት ሲቻል መሆኑን አመላክተዋል።
ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመረጋጋቶችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት፣ ከ4 ሺህ በላይ የሕዝብ ወኪሎች የሚሳተፉበት ሀገራዊ የምክክር ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።
አያይዘውም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች፣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር በሚደረገው ስልጡን ሀገራዊ የምክክር ሂደት ገንቢ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀመንበርና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን አለምነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ በጉልህ የተንጸባረቀበትና የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም አስመስክሯል።
በምርጫ ሂደቱ የታየው የዜጎች ተሳትፎም፣ የፅንፈኛና የባንዳ ኃይሎችን ከንቱ መሻት በማክሸፍ ጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ ውክልና ማግኘታቸውም ከአዲሱ መንግሥት ጋር በብሔራዊ ጥቅምና በሕዝብ አብሮነት ላይ በትብብር የሚሰሩበትን ዕድል እንደፈጠረ አክለዋል።
በክልልና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ ይሁንታ ያገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው በሃሳብ ብዝኅነት የተመሰረተ የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
በመሆኑም የሕዝብ ይሁንታ የተቸራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጣይ ለሕዝብ አብሮነትና ለሁለንተናዊ ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ መፍትሔ በመስጠት፣ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተዘጋጀ ወሳኝ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል።
የኃይል አማራጭ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥልና የልማት ተጠቃሚነትን የሚያቀጭጭ በመሆኑ ለሕዝብ እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች የሰላም አማራጭን መከተል እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።