በክልሉ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና ጥራት እንዲጠናቀቁ የክትትልና ድጋፍ ስራ ይጠናከራል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና ጥራት እንዲጠናቀቁ የክትትልና ድጋፍ ስራ ይጠናከራል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ
ጅግጅጋ፤ ሐምሌ 01/2018(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ የክልሉን እድገት ለማፋጠን የክትትልና ድጋፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ገለጹ።
በሶማሌ ክልል የተጠናቀቀውን የ2018 በጀት ዓመት የሴክተር ቢሮዎች የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በጥራት ተጠናቀው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠን እንዲያግዙ ተገቢ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የክልሉ እና የሀገሪቱን ልማት ማፋጠን የሚችል ብቁ የሰው ሀይል እንዲያፈሩ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በራሳቸው አቅም ገቢና ሀብት በመፍጠር፣ የመደበኛና አጫጭር ሥልጠናዎችን የቅበላ አቅም ለማስፋት የጀመሯቸው የሪፎርም ሥራዎችም እንዲሁ መጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የከተሞች የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ወጥ በሆነ አሠራር እንዲመራ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚያስፈልግ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም የከተሞችን ዕድገት በሚመጥን መልኩ ለመምራት እንዲቻል የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱን በዲጂታል አሠራር ማስደገፍና የከተሜነቱን ኑሮ ማሻሻል ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
የከተሞች አደረጃጀት ገቢን የማመንጨት አቅም በማጎልበት በከተሞቹ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ዜጎችን በሥራ እድል ተጠቃሚ የማድረግ ተግባራት ላይ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በማስገንዘብ።
በመድረኩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሹክሪ፥ በአሁኑ ወቅት በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የአየር ማረፊያዎች፣ ስታዲየሞች እና የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በጥሩ ፍጥነት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በቀጣይም እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት ተጠናቀው ለክልሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የድርሻቸውን ማበርከት እንዲችሉ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የክልሉ ክህሎት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ቢሮ በበኩሉ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ174 ሺህ 340 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን በመድረኩ አንስቷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሀሴን ጋይድ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በማደራጀት ተጠቃሚ የማድረግ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም ለ174 ሺህ 340 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልጸው፤ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማትም ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል አፍርተው ወደ ሥራ ገበያ ማገናኘት እንዲችሉ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።