በሸገር ከተማ ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተድርጓል
ሸገር ፤ሐምሌ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ጤና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በጽሕፈት ቤቱ የማኅበረሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ባለሙያ አቶ ጌታቸው ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት የክረምቱን መግባት ተከትሎ የኅብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት ተድርጓል።
በተለይም በክረምቱ ወቅት የወባ በሽታን ጨምሮ እንደ ኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ እና እንዳይስፋፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እስካሁንም በከተማዋ በሚገኙ የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት ለማኅበረሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም ማኅበረሰቡ በምግብና በመጠጥ ውኃ ንጽሕና አጠባበቅ ረገድ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መከናወኑን አቶ ጌታቸው አንስተዋል።
በዚህም መሠረት የማኅበረሰቡን የአካባቢና የግል ንጽሕና አጠባበቅ ማሳደግ፤ ያቆሩ ውኃዎችን ማፍሰስና ውኃ የሚያቁሩ ጉድጓዶችን የማዳፈን ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ረግረጋማና ውኃ ያቆሩ አካባቢዎችን በመለየት የፀረ-ወባ ኬሚካል የመርጨት ሥራ በሰፊው ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት።
በሽታዎች ከተከሰቱም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል፣ የመድኃኒት አቅርቦትን ጨምሮ አስፈላጊውን ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን ባለሙያው አረጋግጠዋል።