ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን የ50 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር ግብይት ፈጸመ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፈው የበጀት ዓመት የ50 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር ግብይት በመፈጸም በታሪኩ ከፍተኛውን ስኬት ማስመዝገቡን ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መርጊያ ባይሳ አስታወቁ።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መርጊያ ባይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ 214 ሺህ ቶን የግብርና እና የግብርና ያልሆኑ ምርቶች ለገበያ ቀርበው ተገበያይተዋል።

በዚህም ተቋሙ በታሪኩ ያስመዘገበው ከፍተኛው የኢኮኖሚ አፈጻጸም ሆኖ ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፈው የበጀት ዓመት የ50 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር ግብይት በመፈጸም በታሪኩ ከፍተኛውን ስኬት ማስመዝገቡን ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡

ቀደም ሲል ተቋሙ በ2011 በጀት ዓመት ያከናወነው የ40 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ግብይት በከፍተኛ ስኬትነት ይጠቀስ የነበረ ቢሆንም፣ የዘንድሮው የልማት ዕቅድና አፈጻጸም ግን ያንን በላቀ ደረጃ በመብለጥ ስኬታማ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከግብይቱ በተጨማሪ የምርት ገበያው ያስቀመጣቸውን ግቦች በከፍተኛ ሁኔታ መፈጸም የተቻለበት በጀት ዓመት እንደነበረ ገልጸዋል።

ከነዚህም መካከል የመጋዘን ደረሰኝ ብድር በማመቻቸት 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለአርሶ አደሮች፣ ለህብረት ስራ ዩኒየኖችና ለአቀነባባሪዎች ማስተላለፍ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም አርሶ አደሩ ምርቱን አስይዞ ሌላ ተጨማሪ ማስያዣ ሳይፈልግ የአጭር ጊዜ የገንዘብ ፍላጎቱን እንዲያሟላ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የምርት ገበያው ባቋቋመው አካዳሚ አማካኝነት 795 ሰልጣኞችን በቡና ቅምሻ፣ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ጥራት ምርመራ እንዲሁም በአዲስ የኤክስፖርት ማመቻቸት መስክ 46 ሰልጣኞችን ማሰልጠን መቻሉን አብራርተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ቀደም ሲል ሻጮችና ገዢዎች በአካል በመገኘት ብቻ ያከናወኑት የነበረውን ግብይት ሙሉ በሙሉ ወደ ኦንላይን ማዛወር ተችሏል ሲሉ ገልፀዋል።

ይህም ባለድርሻ አካላት ከቤታቸው ወይም ከቢሯቸው ሆነው ያለምንም እንግልት ግብይት እንዲፈጽሙ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የምርት ገበያው የግብርና እና የግብርና ያልሆኑ ምርቶችን ጨምሮ ወደ 28 የሚጠጉ የምርት አይነቶችን ለማገበያየት የሚያስችለውን የውል ማዕቀፍ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

በስንዴ ኢኒሼቲቭ አርሶ አደሮችና ማህበራት ምርታቸውን በመጋዘን ደረሰኝ ብድር በማስያዝ ያለ ገንዘብ እጥረት ማገበያየት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ይህ አሰራር አምራቾችን በፋይናንስ በመደገፍ የገበያ ትስስሩን ያሳለጠ ታላቅ የልማት ስኬት መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም