ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ምርት እና የገንዘብ የመግዛት አቅም በምስራቅ አፍሪካ የቀዳሚነቱን ስፍራ ይዛለች - አይኤምኤፍ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) እና በገንዘብ የመግዛት አቅም በምስራቅ አፍሪካ በቀዳሚነት ስፍራ ላይ እንደምትገኝ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) አስታወቀ።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ 19 ሀገራትን የገንዘብ የመግዛት አቅም (PPP) መሠረት በማድረግ እ.ኤ.አ. በግንቦት 2026 ባወጣው ይፋዊ መረጃ መሠረት፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP በPPP) 558.93 ቢሊዮን ዶላር በመድረስ በምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኢትዮጵያን በመከተል ኬንያ በ435.21 ቢሊየን ዶላር ሁለተኛ፣ ታንዛኒያ ደግሞ በ320.88 ቢሊየን ዶላር ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ምጣኔ ሀብት በአንድ ላይ ሲደመር 1.35 ትሪሊየን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ቀሪዎቹ 16 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በድምሩ ካላቸው አጠቃላይ የኢኮኖሚ መጠን በእጅጉ የሚበልጥ መሆኑ የኢትዮጵያን እና የጎረቤቶቿን የገበያ ግዙፍነት ያሳያል።

ከእነዚህ ግንባር ቀደም ሀገራት በመቀጠል ዩጋንዳ፣ ሱዳን፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን የምጣኔ ሀብት ደረጃ ይዘዋል።

ማዳጋስካር፣ ሩዋንዳ፣ ሞዛምቢክ፣ ማላዊ፣ ሞሪሸስ፣ ሶማሊያ፣ ብሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና ሲሸልስ ደግሞ በቅደም ተከተል ቀጣዮቹ ደረጃዎች ላይ ተቀምጠዋል።

በአንጻሩ ኮሞሮስ በ3.43 ቢሊዮን ዶላር የመጨረሻው 19ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም