ቀጥታ፡

በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው

ሃዋሳ፤ ሐምሌ 1/2018(ኢዜአ)፦በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች እርስ በርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ባከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

"በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ የ2018 ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በሃዋሳ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመርሐግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች እርስ በርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ባከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ተጠቅመው ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ጠቅሰው ይህም ኢትዮጵያዊ አንድነታቸው የሚጠናከርበት ልዩ ዕድል መሆኑንም ተናግረዋል።

በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 25 ሚሊዮን ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች በመሳተፍ ከ53 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ተግባራትን ያከናውናሉ ብለዋል።


 

የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞችም በየአካባቢው ተንቀሳቅሰው በ14 ዘርፎች የተለያዩ ተግባራትን ከማከናወን ባለፈ እርስ በርስና ከሄዱበት ማህበረሰብ የህይወት ልምድና እሴቶችን እንደሚጋሩም አመልክተዋል። 

በተያዘው ክረምት የሚሳተፉ ወጣቶችም ፍቅርን፣ መተሳሰብን፣ ሰላምንና አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ለማድረግ እንዲተጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ በበኩላቸው፤ በጎነትና አብሮነት የማህበረሰቡ መልካም እሴት በመሆኑ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።


 

የለውጡ መንግስት በመደመር እሳቤ ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በህብረተሰቡ ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ሀገራዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የጀመረው ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል፡፡

ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እሴቶችን በማጠናከር ማህበራዊ ሃላፊነትን በጋራ ለመወጣት ሚናው የላቀ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገልጸዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ወጣቶች የሚያከናውኗቸው የልማት ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ከማድረግ ባለፈ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ የወጣቶች ተሳትፎና አቅም ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ አብሮነትንና አንድነትን የማጠናከር ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ለሌሎች ወጣቶች ምሳሌ ከመሆን ባለፈ ለበጎ ፈቃድ ስራዎች ውጤታማነት አበርክቷቸውን እንዲያጠናክሩም አሳስበዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ወጣቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም