ቀጥታ፡

የዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2018(ኢዜአ)፦ ከሐምሌ 8 ጀምሮ ለሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ስታከናውነው የቆየችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት አሁን ላይ የመጨረሻና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

በዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ምክክር የሚካሄድባቸው ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች የተለዩ ሲሆን በእነኚህም ላይ በዝርዝር ለመምከርና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማስቀመጥም፣ ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተወከሉ 4 ሺህ ተመካካሪዎች ወደ አዲስ አበባ በመግባት ላይ ይገኛሉ።


 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና ዳያስፖራ አስተባባሪ አቶ ረታ ጌራ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ ከተለያዩ ክልሎችና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ለዋናው የምክክር ጉባኤ አዲስ አበባ እየገቡ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ለተሳታፊዎቹ በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እና በሌሎችም በተዘጋጁ ምቹ ቦታዎች ላይ አቀባበል እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሄድ ይሆናል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች በበኩላቸው፣ ለዘመናት የዘለቁ አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት በሚደረገው በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ ለመመካከር ዕድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።


 

ይህ ታሪካዊ ምክክር ይበልጥ የበለጸገች፣ የተረጋጋች ሀገር ለመገንባት አስተማማኝ መሠረት የሚጥል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ወሳኝ ወቅት ተመካክረን፣ ተስማምተንና ተቀራርበን ጠንካራ ሀገር ለሚመጣው ትውልድ ለማስተላለፍ ትልቅ ተስፋ ሰንቀናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም