ቀጥታ፡

በአፍሪካ ቀዳሚና ተወዳዳሪ የሆነ የጥራት ማረጋገጫ ተቋም ተገንብቷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2018(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ቀዳሚና ተወዳዳሪ የሆነ የጥራት ማረጋገጫ ተቋም መገንባቱን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መዓዛ አበራ ገለጹ፡፡

ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ ከ36 ሺህ በላይ የምርት ጥራት ማረጋገጫ አገልግሎቶችን መስጠት መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መዓዛ አበራ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ድርጅቱ በተደራጁ የፍተሻ ላቦራቶሪዎቹ አማካኝነት የምርትና የአገልግሎት ጥራት የማረጋገጥ፣ የምርትና የስራ አመራር ሰርተፊኬሽን እንዲሁም የኢንስፔክሽን አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ድርጅቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመቱ ከ36 ሺህ በላይ የምርት ጥራት ማረጋገጫ አገልግሎቶችን መስጠቱን አስታውቀዋል።


 

በበጀት ዓመቱ የተሰጠው የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ5 ሺህ 500 በላይ አገልግሎቶች እድገት ያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል።

የድርጅቱን ተደራሽነት ለማስፋትና አገልግሎቱን ወደ ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ በተሰራው ሰፊ ስራ በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያ የሆነውን የነዳጅ፣ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች ፍተሻ ላቦራቶሪ ስራ ማስጀመሩንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአዳማ ቅርንጫፍ ባለ አምስት ወለል ህንጻ በማስገንባት በምግብ፣ መጠጥና በግብርና ግብዓቶች ላይ ተጨማሪ የፍተሻ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን በደሴና ኮምቦልቻ ያሉ ቅርንጫፎችንም የማዘመን ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በምርትና ስራ አመራር ሰርተፊኬሽን ዘርፍ ከ900 በላይ ድርጅቶች የምርት ጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲገቡ በጅቡቲ ወደብ የጅምላ ጭነት ኢንስፔክሽን አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

መንግስት የምርትና የአገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅ የጀመረው ሰፊ የሪፎርም ስራ ለተቋሙ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውቀዋል።


 

ይህ የተከናወነው የሪፎርም ስራ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለችው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እና ለመቀላቀል በድርድር ላይ ካለችበት የዓለም ንግድ ድርጅት አንጻር የሀገሪቱን የንግድ ልውውጥና ኢኮኖሚ ለማሳደግ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ጥራታቸውን ያልጠበቁ የውጭ ምርቶች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ለመከላከልና የሀገር ውስጥ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትልቅ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

በዚህም በአፍሪካ ቀዳሚና ተወዳዳሪ የሆነ የጥራት ማረጋገጫ ተቋም መገንባቱን ዋና ዳይሬክተሯ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም