በጋምቤላ ክልል የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየተሰጠ ነው
ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- በጋምቤላ ክልል ሀገር አቀፉ የ12ኛ ክፍል ፈተና በተሳካ ሁኔታ እየተሰጠ እንደሚገኝ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ አራት ሺህ የሚጠጉ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን ተቀብሎ በበይነ መረብና በወረቀት በማስፈተን ላይ መሆኑን ገልጿል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡኩኝ ኦኬሎ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ ሀገር አቀፉ የ12ኛ ክፍል ፈተና ስኬታማ በሆነ መልኩ እየተሰጠ ይገኛል።
በክልሉ በዘንድሮው ዓመት ከ8 ሺህ 530 በላይ የተፈጥሮና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን በበይነ መረብና በወረቀት በማስፈተን ሂደት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ሲሰጥ የቆየው የ1ኛ እና 2ኛ ዙር የበይነ መረብ ፈተና በስኬት መጠናቀቁን ጠቁመው፤ በዛሬው በ3ኛው ዙር የፈተና መርሃ ግብርም ከበይነ መረብ በተጨማሪ በወረቀት ለሚፈተኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ጭምር ፈተናው እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ፈተናው እየተሰጠ ያለው በጋምቤላና በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲዎች፤ እንዲሁም በጋምቤላ ከተማ ኢሌይና ብርሃን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆኑን ጠቁመው፤ በእስካሁኑ ሂደት ፈተናው ስኬታማ በሆነ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፓል ቦት (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው 3 ሺህ 995 የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን ተቀብሎ በበይነ መረብና በወረቀት እያስፈተነ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች አስፈላጊውን የምግብ፣ የመኝታና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ጠቀመው፤ የ3ኛው ዙር ፈተና እንደተጠናቀቀም 3 ሺህ 420 የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን ተቀብሎ በተመሳሳይ መልኩ እንደሚያስፈትን ተናግረዋል።