የህገ-ወጡ የህውሃት ቡድን የአስገዳጅ አፈሳ እና የእገታ ድርጊቶች የቡድኑን ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ ማክተሙን ያመላከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህገ-ወጡ የህውሃት ቡድን የአስገዳጅ አፈሳ እና የእገታ ድርጊቶች የቡድኑን ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ ማክተሙን ያመላከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2018(ኢዜአ)፦ የህገ-ወጡ የህውሃት ቡድን የአስገዳጅ አፈሳ እና የእገታ ድርጊቶች የቡድኑን ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ ማክተሙን ያመላከተ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ገለጹ።
በትግራይ ክልል የተለያዩ የግል ጥቅሞችንና ፍላጎቶችን ለማሳካት ሲባል በሕዝቡ ላይ የሚፈጸመው አስገዳጅ የአፈሳ እና የእገታ ድርጊቶች በከፍተኛ ሁኔታ መቀጠላቸውን ጋዜጠኞቹ ገልጸዋል።
ድርጊቱ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፤ የክልሉ ማኅበረሰብም ለእነዚህ አካላት የነበረውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ መንፈጉን ያመላከተ ነው ብለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል የአውራምባ ታይምስ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እንደገለጸው፤ ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉ አካላት ከወርቅ እና ማዕድን ንግድ ጋር የተያያዙ በርካታ የግል ጥቅሞች አሏቸው ብሏል።
እነዚህን ጥቅሞች ለማስጠበቅ ሲባልም ተፈናቃዮችን ለማስመለስ የሚሉ ምክንያቶችን እንደ ሽፋን ወይም ማስተባበያ እየተጠቀሙ ይገኛሉ ሲል ጠቅሷል።
እነርሱ ለሰከንድም ቢሆን ስለሕዝቡ ይጨነቃሉ ብዬ አላስብም ያለው ጋዜጠኛ ዳዊት፤ አሁን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በማኅበረሰቡ ዘንድ ውድቅ መደረጉን ገልጿል።
በዚህም ምክንያት ወጣቶችን በኃይል ወደ ማሰልጠኛዎች ማስገባትና አስገዳጅ አፈሳዎችን ማካሄድ መጀመራቸውን ጠቁሟል።
አሁን ላይ ድርጊቱ ተባብሶ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን ጭምር በማስቆም ወጣቶችን የማስቀረት ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም እጅግ የሚያሳዝን ሁኔታ መሆኑን አብራርቷል።
ጋዜጠኛ ሄርሞን ፍቃዱ በበኩሏ፤ የሕወሃት ጽንፈኛ አመራሮችና የጥፋት ኃይሎች እየፈጸሙ ያሉትን ድርጊት በጽኑ አውግዛለች።
በአሁኑ ዘመን የፕሮፓጋንዳ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲባል ሰዎችን በግድ ማገትና ማፈስ የማይጠበቅና እጅግ የወረደ ድርጊት መሆኑን ገልጻለች።
የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አብረሃም ፅጌ፣ ይህ ቡድን ከቀደመው ስህተቱ መማር አለመቻሉን ገልጿል።
ሕዝቡ አሁን ላይ ያለፈው ይበቃናል ከዚህ በኋላ ዳግም ስህተት ውስጥ አንገባም በማለቱ የቡድኑ ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ ማክተሙን አስታውቋል።
አሁን ከሕዝቡ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ በማጣታቸው ምክንያት አስገዳጅ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ እንደሚገኙ ተናግረው፤ ይህ የሚያሳየው ሕዝቡ እንዳልተቀበላቸው ያመላክታል ብሏል።
ድርጊቱን እየፈጸመ ያለው ቡድን በትግራይ ሕዝብ ዘንድ የነበረውን ተቀባይነት ካጣ መቆየቱን ጠቁሞ፤ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ማጣታቸውን ገልጿል።