ቀጥታ፡

በኮሚሽኑ የተለዩት የምክክር አጀንዳዎች ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው

ወላይታ ሶዶ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተለዩት የምክክር አጀንዳዎች ሁሉንም አካታች አድርገው የተመረጡና ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን የሚፈታ በመሆኑ ዕድሉን መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምክክሩ ሂደት ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጀምሮ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አጀንዳ የተለየበት መሆኑን ጠቁመው፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ጠቃሚ ሒደት ነው ብለዋል።

የምክክሩ ዋና ዓላማ ባለፉት ዘመናት ለቅራኔ ምንጭ የሆኑና የተከማቹ ችግሮችን በጋራ መክሮ መልክ ማስያዝ እንደሆነ ጠቅሰው፣ አዲስ ማህበራዊ ውል የሚፈጸምበት መሆኑንም አመልክተዋል።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም በኮሚሽኑ የተለዩት የምክክር አጀንዳዎች ሁሉንም አካታች አድርገው የተመረጡና ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ተሻለ ተገኔ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በኮሚሽኑ የተለዩ ስምንት የምክክር አጀንዳዎች ለቅራኔ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ናቸው።

ባለፉት ጊዜያት የተከማቹ ችግሮችን በጋራ መክሮና ተወያይቶ መፍታት የሕዝቦችን አንድነት በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

አለመግባባቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፍታት የስልጣኔ መገለጫ ከመሆኑም ባለፈ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማምጣት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል።

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት ያከናወናቸው ተግባራት ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ሀገርን በጽኑ መሰረት ለማቆም ምቹ መደላድል የሚፈጥር በመሆኑ ይህን ታሪካዊ ዕድል መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ የሁሉም የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክር የዜጎችን አንድነት በማጠናከር ለሀገራቸው በጋራ እንዲቆሙ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጣሰው ታደሰ ናቸው።

ወደ መጨረሻ ምዕራፍ የተሸጋገረው ሀገራዊ ምክክር በሀገሪቱ ለቅራኔ ምንጭ የሆኑና ለዘመናት ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ዋና ዋና ችግሮችን በጋራ መክሮ ለመፍታት በወሳኝ ጊዜ የተነሳ መሆኑንም ተናግረዋል።

ምክክሩ ለኢትዮጵያ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት አስፈላጊ በመሆኑ ዕድሉን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አንስተዋል።

ታሪካዊ ዕድሉን ማባከን እንደማይገባ ገልጸው፣ አለመግባባቶችን በዘላቂነት በመፍታት ለሁሉም የምትመች ሀገር ለማጽናት ከሁሉም ቅንነት የተሞላበት ተሳትፎ ይጠበቃል ብለዋል።

ምክክር የስልጣኔ መገለጫ ከመሆኑም ባለፈ ሁሉንም አሸናፊ በማድረግ ጠንካራ አንድነትና ሀገረ መንግስት ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ስኬታማ እንዲሆን በምክክር ወቅት "የእኔ ብቻ ይሰማ" ከሚለው አስተሳሰብ መውጣት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም