ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን በግብርናው ዘርፍ የተገኘው አበረታች ውጤት ተጠናክሮ ይቀጥላል

ደሴ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ወሎ ዞን በግብርናው ዘርፍ ቴክኖሎጂንና አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የተገኘው አበረታች ውጤት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮነን ገለፁ።

በዞኑ 15 የእርሻ ትራክተሮች  ለአርሶ አደሩ ተከፋፍለዋል።


 

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮነን በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ በዞኑ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዘግቦበታል።

ዞኑ በሜካናይዜሽን ለሚካሄድ የሰብል ልማት ምቹ መሆኑን ጠቁመው፣ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት ለማስቀጠልም 15 የእርሻ ትራክተሮችን ለወረዳዎች ማስረከብ መቻሉን አስረድተዋል።

በዚህም በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ጥራትና ብዛት ያለው ምርት በማምረት ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው፣ በዞኑ ግብርናውን ከኋላ ቀር አሰራር  በማውጣት ወደ ዘመናዊ የአስተራረስ በዘዴ በመከተል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።


 

በዚህም አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማምረት የሚያስችል አቅም መፍጠሩን ተናግረዋል።

ይህም የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችንና አዳዲስ አሰራሮችን በተገቢው ሁኔታ በመተግበር የመጣ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።

የመጣውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠልም ዛሬ የተሰራጩትን ጨምሮ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 37 የእርሻ ትራክተሮችን በማሰራጨት በአጠቃላይ በዞኑ ያሉ የትራክተሮች ቁጥርን 89 መድረሱን አረጋግጠዋል።

"በዘመናዊና የተሻሻለ የግብርና አሰራር ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል" ያሉት ደግሞ የለጋምቦ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን ሙላት ናቸው።


 

አርሶ አደሩ ሜካናይዜሽን አሰራርን እየተላመደ በመምጣቱ የቴክኖሎጂ ጥያቄው መስፋቱን ጠቁመው፣ ዛሬ የተረከቧቸውን ሁለቱን ጨምሮ 15 ትራክተሮች በስራ ላይ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።

በርክክቡ ወቅት  በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፤የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ እና ሌሎች አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም