ቀጥታ፡

ለምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎች በአሰባሳቢ ትርክት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚያስችሉ ናቸው

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- ለምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎች የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታት በአሰባሳቢ ትርክት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚያስችሉ አንኳር ነጥቦች መሆናቸውን የአማራ ክልል ሴቶች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ማካሄድ የሚጀምር ይሆናል።

በምክክር ኮሚሽኑ በተለዩት ስምንት አንኳር አጀንዳዎች ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ይመካከራሉ።

የአማራ ክልል ሴቶች ማህበራት ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ እንየ ገነቱ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ታሪካዊ እድል መሆኑን አንስተዋል።

ለምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎች የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታት በአሰባሳቢ ትርክት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚያስችሉ አንኳር ነጥቦች መሆናቸውን በመግለጽ፤ በጉዳዮቹ ላይ ተመካክረን መፍትሄ ለመሻት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲንከባለሉ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመቋጨት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት የምንችልበት መልካም እድል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ማህበራት ፌዴሬሽን በምክክር ሂደቱ እስካሁንም በንቃት መሳተፉን አውስተው በቀጣይም ለምክክር ጉባኤው መሳካት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ብለዋል።

የምክክር ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ጥረት ከማድረግ ባሻገር ሴቶችና ህጻናት መብታቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ የሚያስችል አውድ እንዲፈጠር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም