ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ለዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች ስኬት የመንግስትን ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት ያረጋገጠ ነው

ሰመራ፤ ሐምሌ 1/2018(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትላንትናው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰጡት ማብራሪያ ለዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች ስኬት የመንግስትን ቀጣይነት ያለው ትጋትና ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑን በአፋር ክልል የሰመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም መንግስት በተለይም ለዘላቂ ሰላም፣ ለንግግርና ውይይት ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።

የግጭትና ጦርነት እሳቤ አውዳሚና ትርፍ የሌለው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያስፈልገን ሰላም፣ ትብብር እና አብሮነት ነው ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ለዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች ስኬት የመንግስትን ቀጣይነት ያለው ትጋትና ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ዋሲሁን አያሌው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ተገኝተው የሰጡት ማብራሪያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን የዳሰሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የሰላም ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን በማንሳት የግጭትና ጦርነት እሳቤ አውዳሚና ትርፍ የሌለው በመሆኑ የሰላም ጥረታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸው መንግስት ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የትኛውንም ችግር በውይይትና በንግግር መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት የሰጠ በመሆኑ ሁላችንም የሰላምን ጉዳይ የራሳችን አጀንዳ አድርገን መስራት አለብን ነው ያሉት።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ሙሳ መሐመድ በበኩሉ፥ ባለፉት አምስት ዓመታት ሁላችንንም ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተሰርተዋል ይህንንም በበቂ ማሳያዎች መግለጽ ይቻላል ብሏል።

በመሆኑም በልማት የተገኘውን ስኬት በሰላም ግንባታም በመድገም ለሁለንተናዊ እድገትና የጋራ ተጠቃሚነት መስራት ይገባናል ሲል ገልጿል።

አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ በማድረግ፣ በከተሞች አካባቢ ቀልጣፋ የአገልግሎት ተጠቃሚነትን በፍጥነት ማሳደግ መቻሉን የገለጹት ደግሞ አቶ ረምዚ ይማም ናቸው።

የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድም አሁን ባለው ሁኔታ እየተከናወኑ ያሉት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በትምህርት ዘርፉ በርካታ ሞዴል ትምህርት ቤቶች መገንባታቸን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገባ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም