በምዕራብ ወለጋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ470 በላይ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ470 በላይ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል
ጊምቢ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ከ470 በላይ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፋ ገለጹ።
ዋና አስተዳዳሪው እንደተናገሩት፤ ለአገልግሎት የበቁት እነዚህ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች የተገነቡት ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ነው።
በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተጠናቀው ወደ ሥራ ከገቡት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተቋማት፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ማኑፋክቸሪንግ ሼዶች፣ የመስኖ ልማት መሠረተ ልማቶች፣ የገጠርና የከተማ መንገዶች እንዲሁም የጤና ኬላዎች እና የትምህርት ተቋማት ናቸው ብለዋል።
የእነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባት በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም ከማጽናት ባለፈ፣ ሕዝቡ ልማቱን በማፋጠን የራሱን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በንቃት እንዲያሳልጥ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
የዞኑ ነዋሪዎች በበኩላቸው ፤ በአካባቢው የተገነቡት ፕሮጀክቶች የሕዝቡን የቆየ የመልማት ፍላጎት በትክክል የመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ የተገነቡት የትምህርትና ጤና ተቋማት በቅርበት አገልግሎት እንድናገኝ እያስቻሉን ነው፤ ይህም ገንዘብና ጉልበታችንን በመቆጠብ በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ እንድንተጋ አግዞናል ብለዋል።
እንዲሁም በአካባቢያችን የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ምርታችንን በቀላሉ ወደ ገበያ በማድረስ ተጠቃሚ እንድንሆን እያገዘን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የአካባቢያችንን ሰላምና ልማት ዘላቂ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከምንጊዜውም በላይ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።