በአቮካዶ ምርት የተመዘገበውን ስኬት በቆላ ፍራፍሬ ልማት ለመድገም እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአቮካዶ ምርት የተመዘገበውን ስኬት በቆላ ፍራፍሬ ልማት ለመድገም እየተሰራ ነው
ገንዳ ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- የአቮካዶ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ እየተመዘገበ ያለውን ስኬት በሌሎች የቆላ የፍራፍሬ ልማቶች ለመድገም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዞኑ በገንዳውኃ ጊዮርጊስ ተፋሰስ ተጀምሯል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊና ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ ጌጡ እንደገለጹት ፤ለዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ችግኞች በማዘጋጀት የተከላ ስራ ተጀምሯል።
ለተከላ የተዘጋጁት ችግኞችም ለምግብነት የሚውሉ፣ ቀጥተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የደን ዝርያዎችና ለእንስሳት መኖ የሚውሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ለቆላ ፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹ የአየር ንብረት፣ ለም መሬትና ከፍተኛ የውሃ አማራጭ በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
"ለፍራፍሬ ልማት ቀደም ብለን ተዘጋጅተናል" ያሉት ኃላፊው ከ200 ሺህ በላይ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች በክላስተር መዘጋጀቱን ጠቁመው ከ600 ሺህ በላይ የሙዝ፣ ማንጎ ፣ ዘይቱን ፓፓያና ብርቱካን ችግኞች ይተከላሉ ብለዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በበኩላቸው “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ላይ የዞኑ ሕዝብ በንቃት በመሳተፍ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ አሳስበዋል።
ችግኞችን ከመትከል ባለፈ፣ በዘላቂነት ፀድቀው ለታለመላቸው ፍሬ እንዲበቁ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉት ወጣት አሸናፊ ታፈረና ደጉ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው፣በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣታቸውን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
እየተገኘ ያለውን ጥቅም ለማሳደግም በክረምቱ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያለምንም ቀስቃሽ በፈቃዳቸው በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን አስረድተዋል።
በማስጀመሪያው መርሐግብሩ ላይ የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች፣ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።