በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማነቃቃትና በመደገፍ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማነቃቃትና በመደገፍ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ ነው
አሶሳ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማነቃቃትና በመደገፍ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ መሆኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ሙሐመድ ኢብራሂም ገለጹ።
ኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ እየሰራች ትገኛለች።
ከእነዚህም መካከል በታዳሽ ኃይል ማመንጫ፣ በታላላቅ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም በከተማ ውበትና በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ሰፊ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እየተገነቡ ይገኛሉ።
እነዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በሚገነቡበት ወቅት በርካታ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን በማሳደግና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ የጎላ ሚና እንዳላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።
ትናንት በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምራ በማጠናቀቅ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት በአሁኑ ወቅት የጀመራቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የፕሮጀክቶቹ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ፋይዳ በምሁራንና በባለሙያዎች ዘንድ ሰፊ ትኩረት እየተሰጠው ይገኛል።
ፕሮጀክቶቹ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያሻሽሉ እና የኢትዮጵያን ጀምሮ የመጨረስ አቅም በይፋ የሚያረጋግጡ እንደሆኑ አንስተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ሙሐመድ ኢብራሂም እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዝሃ ዘርፍ ላይ ያተኮረ መሆኑ በሁሉም ዘርፎች ተመጣጣኝ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ አግዟል።
በተለይም ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የሚያመነጩት ገቢ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍ ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያሳዩ እንደሆነ ጠቁመው፤ ይህም የሀገሪቷን ገቢ እና ወጪን በማስተካከል ጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል።
ይህም የሀገሪቷ ዓመታዊ በጀት በየጊዜው ጭማሪ እንዲያሳይ እንዲሁም ፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅም እንዲያድግ አይነተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ እና በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ያከናወነቻቸው የሪፎርም ተግባራት ሀገሪቱን በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ባለቤት እንደሚያደርጋትም ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ "ብሪክስን" ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የጀመረችው የንግድ ግንኙነት እና የወጪ ንግድ መጨመር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ እንደሆነም አንስተዋል።