ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በ53 ማዕከላት እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ 53 ማዕከላት በማስፋፋት፣ ለማህበረሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የመንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ይቀርፋል ተብሎ ወደ ስራ የገባው ይህ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች እየተስፋፋ ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው ይኸው አገልግሎት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ እየሆነ መምጣቱንና የአገልግሎት አሰጣጡም ፈጣንና ቀልጣፋ መሆኑ ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳምጠው ገመቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በ2018 በጀት ዓመት አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ በማድረግ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ ምላሽ ለመስጠት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። 


 

በቴክኖሎጂ በመታገዝ በአምስት ዋና ዋና ከተሞች የተጀመረውን አሰራር በማስፋፋት፣ አሁን ላይ በክልሉ በሁሉም ዞኖች 53 ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አስረድተዋል።

በማዕከላቱ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት ይበልጥ ለማሻሻልና ተጠቃሚነቱን ለማስፋትም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በአገልግሎቱ አማካኝነት ህብረተሰቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈልገውን ጉዳይ ማሳካት ችሏል፤ ይህም ዜጎችን ከእንግልትና ካልተገባ ወጪ ከመታደጉም ባለፈ፣ ጊዜና ጉልበታቸውን በአግባቡ በልማት ስራዎች ላይ እንዲያውሉ አስችሏል ነው ያሉት።

ይህ አሰራር በክልሉ የአገልግሎት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ መሻሻል እያስገኘ እንደሚገኝ የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ በተለይም አገልግሎቱ በአንድ ማዕከል የተደራጀ፣ ፈጣን፣ ምቹና ግልጽነት ያለው በመሆኑ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን በተሻለ ሁኔታ እያነቃቃው መሆኑን አክለዋል።


 

በአገልግሎቱ የህብረተሰቡን እርካታ ጭምር ከፍ ማድርግ መቻሉንና እስካሁንም ከ700 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ዳምጠው ጠቁመዋል።

ማዕከላቱ ከዞኖች ባለፈ ወደ ወረዳዎችም ተደራሽ እየሆኑ በመሆኑ፣ በቀጣይ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች አገልግሎቱን ለማድረስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

ከዚህም በተጨማሪ በቀጣይ የዲጂታላይዜሽን አሰራርን ሙሉ በሙሉ እውን በማድረግ፣ ህብረተሰቡ አገልግሎቱን ባለበት ሆኖ በኦንላይን (Online) ማግኘት እንዲችል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም