ቀጥታ፡

በባሌ ዞን በበጀት ዓመቱ ከ700 በላይ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት ተሸጋግረዋል

ሮቤ ፤ ሐምሌ 1/ 2018 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በበጀት ዓመቱ 719 ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩ አርሶ አደሮችና ማኅበራት የተደረገላቸው ማበረታቻ ለተሻለ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ገልጸዋል።

የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ኢብሮ እንዳሉት፤ በዞኑ አርሶ አደሩ በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን መዋቅራዊ ሽግግር እንዲያደርግ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

በዚህም በዞኑ እየተገባደደ በሚገኘው የበጀት ዓመት 719 የሚሆኑ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ከግብርና ወደ ኢንቨስትመንት በመሸጋገር የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ሥራ ውስጥ መግባታቸውን አመልክተዋል።

አርሶ አደሮቹና ኢንተርፕራይዞቹ ባለፉት ዓመታት በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ ከመሆን ባሻገር በነፍስ ወከፍ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹና ማኅበራቱ ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት ባስመዘገቡት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል መሆኑንም አስረድተዋል።

የተሸጋገሩት አርሶ አደሮች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ14 ሺሕ 400 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አክለዋል።

ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ከተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች መካከል ማኑፋክቸሪንግ፣ አገልግሎት፣ ኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች ይገኙበታል ብለዋል።

ለተሸጋገሩ አርሶ አደሮች በተሰማሩበት የሥራ መስክ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የመሬት አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች የብድርና የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደሚደረግላቸውም ተናግረዋል።

አቶ መሐመድ እንዳሉት፤ በዞኑ ባለፉት ዓመታት በግብርናው ዘርፍ የተከናወነው ውጤታማ ሥራ የተሸጋገሩ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች የግብርናው መስክ ሽግግር አዎንታዊ ማሳያዎች መሆናቸውን አክለዋል።


 

ወደ ኢንቨስትመንት ከተሸጋገሩ አርሶ አደሮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ከድር፤ በግብርና ሥራ በመሰማራት በሚያመርቱት ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ውጤታማ በመሆን ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ ምርጥ ዘር ብዜት ሥራ ለመሰማራት የሚያስችል የኢንቨስትመንት መሬት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በግብርና ዘርፍ ባከናወኑት ውጤታማ ሥራ ከተሰጣቸው የእውቅና ሰርተፊኬት ባሻገር በኢንቨስትመንት ማበረታቻነት ያገኙት የመሥሪያ ቦታ ለተሻለ ስራ እንደሚያነሳሳቸው የገለጹት ደግሞ አቶ በያን መሐመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም