ስዊዘርላንድ ከ72 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ስዊዘርላንድ ከ72 ዓመታት በኋላ ለዓለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ አለፈች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/ 2018 (ኢዜአ):- በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የ16ቱ የጥሎ የመጨረሻ ማለፍ መርሐ ግብር ስዊዘርላንድ ኮሎምቢያን በመለያ ምት አሸንፋለች።
ማምሻውን በቢሲ ፔሌስ ቫንኩቨር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ይህንንም ተከትሎ 30 ደቂቃ የተጨመረ ሲሆን ግብ ባለመቆጠሩ ምክንያት ወደ መለያ ምት አምርቷል።
በዚህም ስዊዘርላንድ 4 ለ 3 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብታለች።
ስዊዘርላንድ ከ72 ዓመታት በኋላ ለሩብ ፍጻሜ አልፋለች። በታሪኳ ለአራተኛ ጊዜ ስምንት ውስጥ ገብታለች።
በሩብ ፍጻሜው ከአርጀንቲና ጋር ትጫወታለች።
የደቡብ አሜሪካዋ ኮሎምቢያ በዓለም ዋንጫ ለሁለተኛ ጊዜ ለሩብ ፍጻሜ የማለፍ ህልሟ አልተሳካም።
አጠቃላይ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሳቢ ያልነበረ እና የግብ እድሎች በበቂ ሁኔታ ያልተፈጠሩበት ነበር።
ጨዋታውን ተከትሎ የ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ተጠናቋል።
የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ከሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳሉ።
ፈረንሳይ ከሞሮኮ፣ ኖርዌይ ከብራዚል፣ ስፔን ከቤልጂየም እና አርጀንቲና ከስዊዘርላንድ በሩብ ፍጻሜው የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው።