ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የገነባችው አስተማማኝ የፀጥታ ተቋም የታሪካዊ ጠላቶችን ከንቱ መሻት በማክሸፍ ሁለንተናዊ ብልፅግናን በሚያረጋግጥ የስኬት ምዕራፍ እንድትጓዝ እያደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የገነባችው አስተማማኝ የፀጥታ ተቋም የታሪካዊ ጠላቶችን ከንቱ መሻት በማክሸፍ ሁለንተናዊ ብልፅግናን በሚያረጋግጥ የስኬት ምዕራፍ እንድትጓዝ እያደረገ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው፣ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ መንግሥት ሁልጊዜም ቢሆን ለሰላም ያለው በር ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል ከምንጊዜውም በላይ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊትም በላቀ ቴክኖሎጂና የሰው ሃይል በጽኑ መሰረት መገንባቱን አብራርተዋል።

ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ ጽንፈኛ ኃይሎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ሀገሪቱን ለማተራመስ ቢሞክሩም ፍላጎታቸው እንደማይሳካ ገልጸዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሳዲቅ አደም እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን መረጋጋት፣ ዕድገትና ሰላም የማይሹ ታሪካዊ ጠላቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊትና በየደረጃው ያለው የጸጥታ መዋቅር እየከፈለው ባለው መስዋዕትነት በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም ማስፈን መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ የገነባችው አስተማማኝ የፀጥታና ደኅንነት ተቋም የታሪካዊ ጠላቶችን ከንቱ መሻት በማክሸፍ ሁለንተናዊ ብልፅግናን በሚያረጋግጥ የስኬት ምዕራፍ እንድትጓዝ እያደረገ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም ያላት ደረጃ እና ሚና ከፍ እንዲል ሕብረተሰቡ በሰላም ዙሪያ በነቂስ መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

ሁሉም በተሰማራበት መስክ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ጥረት ማድረግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል መስፍን እርካቤ በበኩላቸው፤ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እንዲሁም ኢኮኖሚው እንዲያድግ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት አሁንም ለሰላም የዘረጋው እጅ አለማጠፉ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ አለመግባባቶችን በውይይት ብቻ የመፍታት ሂደት መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም