ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ እመርታዊ ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ እመርታዊ ውጤት እያስገኘ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዮሐንስ ፋንታ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ከፍተኛ የኤክስፖርትና የዲፕሎማሲ ፎረም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገራት ዲፕሎማቶች፣ የኢትዮጵያ ላኪዎች፣ አምራቾችና ባለድርሻ አካላት መተገኙበት እየተካሄደ ነው።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዮሐንስ ፋንታ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ተከታታይነት ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ለጠንካራ የንግድ ኢንቨስትመንትና ለቀጣናዊ ትስስር ማዕከል ለመሆን ምቹ ሁኔታ ያላት መሆኗን ገልጸዋል።

ይህም የወጪ ንግድን ለማጠናከርና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዲፕሎማሲ የኢኮኖሚ ግንኙነቶችንና አጋርነት የሚጠናከርበትና ዘላቂ ልማት በተግባር የሚረጋገጥበት ስትራቴጂያዊ መሣሪያ መሆኑንም አክለዋል።

በዚህም መሰረት መንግሥት ኢትዮጵያን በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የፎረሙ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ምርቶች፣ አገልግሎቶችና የኢንቨስትመንት አማራጮች ለዓለም አቀፍ አጋሮች ማስተዋወቅ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት የጀመረው የሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፉ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለመዳሰስና ለባለሃብቶች ለማስተዋወቅ ፎረሙ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዘጋጀው መድረክ የኢትዮጵያን ምርቶችና አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ለማስተዋወቅ ጠንካራና ይበልጥ የተቀናጀ አሰራር ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም