የህወሃት ጽንፈኛ አመራሮች የክልሉን ሕዝብ ለስቃይ ለማጋለጥ እየተንቀሳቀሱ ያለበትን ሁኔታ መቀልበስ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃት ጽንፈኛ አመራሮች የክልሉን ሕዝብ ለስቃይ ለማጋለጥ እየተንቀሳቀሱ ያለበትን ሁኔታ መቀልበስ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ የህወሃት ጽንፈኛ አመራሮችና የጥፋት ኃይሎች የክልሉን ሕዝብ ለዳግም ጥፋትና ስቃይ ለማጋለጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ መቀልበስ ይገባል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ።
ሴንተር ፎር ሪስፖንሲብል ኤንድ ፒስፉል ፖለቲካ (CRPP) ከትግራይ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (TBS) ጋር በመተባበር “ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት በትግራይ፡ የብዙሃን መገናኛ እና የማህበረሰብ አንቂዎች ሚና” በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና የማህበረሰብ አንቂዎች ተገኝተዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አሁን ጊዜው የትግራይን ሰላም ማዕከል አድርጎ በቁርጠኝነት መሥራት ያለበት ወቅት ነው ብለዋል።
በሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች የሚታዩ የልማት እንቅስቃሴዎች በትግራይም መከናወን እንዳለባቸው አመልክተው፤ ሰላም ላይ በትኩረት መሥራትና የክልሉን ሕዝብ ህልውና ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የተወሰኑ የህወሃት ጽንፈኛ አመራሮችና የጥፋት ኃይሎች የክልሉን ሕዝብ ለዳግም ጥፋትና ስቃይ ለመዳረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ሁኔታ መላው ኅብረተሰብ በጋራና በአንድ ድምፅ በመቆም እንዲቀለብሰው ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ቡድን ካለፈው ጥፋቱ ሳይማር ሕዝቡን ወደ አዲስ መከራ ለመክተት እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዳይፈጸምና ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ እያደረጉ ያሉት እራሳቸው ሆነው ሳለ፣ መልሰው ስምምነቱ አልተፈጸመም እያሉ ይከሳሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ለሰላሳ ዓመታት ወጣቶችንና ሕፃናትን ወደ ካምፕ ከሚያስገባው ሻዕቢያ ልምድ በመውሰድ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ማስቆም አለብን ብለዋል።
የፌዴራል መንግሥት ተፈናቃዮችን ለመመለስ ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለው በመግለፅ፤ ነገር ግን ከጦርነትና ከተፈናቃዮች ስቃይ ማትረፍ የለመዱ እነዚህ አካላት የሰላም ሂደቱን እያስተጓጎሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ወጣቱን በማስገደድ ወደ ዳግም ጦርነት በመክተት የሕዝብን መከራ የሚያራዝሙ አካላት ይብቃችሁ ሊባሉ እንደሚገባ ያሳሰቡት ሚኒስትሩ፤ በትግራይ ወጣቶች ላይ የሚያደርሱትን ማፈንና ማፈናቀል ሊያቆሙ እንደሚገባ ተናግረዋል።