በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርና በማጎልበት ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርና በማጎልበት ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርና በማጎልበት ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) አባል አገራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርና ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት አውደ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል።
በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ በግብርና ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ዜና ሀብተወልድ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርና ለማስፋፋት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።
የመስኖ ስንዴ ልማት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የአፈር መሸርሸርን መከላከልና ጤንነትን የመጠበቅ፣ የእንስሳት ምርታማነትን የማሻሻያና ሌሎች ስራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርና ለማጎልበት የተገኙ ውጤቶች ለኢጋድ አባል ሀገራት ተሞክሮ የሚውሉ መሆናቸውን አመልክተው፤ በቀጣናው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የግብርና ልህቀት ማዕከል ለማቋቋም ግብዓት እንደሚሆን አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ስራዎች በአንድ ሀገር ብቻ የሚከናወን ሳይሆን የአገራት ቅንጅት የሚያስፈልግ በመሆኑ ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) ጋር የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢጋድ አባል ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም አኳያ ያሉበት ደረጃ ላይ ያተኮረ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።
በአውደ ጥናቱ ውይይት የሚቀርበው ጥናት የአባል አገራትን የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና የልህቀት ማዕከላትን ለማቋቋም፣ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር፣ የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርናን የመቋቋም አቅምን ለመገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ) የግብርና እና አካባቢ ጥበቃ ዳይሬክተር ዳሄር ኤልሚ በመወከል የኢጋድ የፖሊሲና የምግብ ዋስትና ኤክስፐርት ሲልቪያ ሄንጋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የአየር ንብረት ለውጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አምራች አርሶ አደሮችን እየጎዳ ይገኛል ።
የሙቀት መጠን መጨመር፣ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋዎች፣ የመሬት መራቆት፣ የምግብ ዋስትናና ሌሎች ችግሮች የኢኮኖሚ እድገትን እና ዘላቂ ልማትን እያደናቀፉ ይገኛሉ ብለዋል።
በመሆኑም፣ የመቋቋም አቅም ያለው ግብርና፣ ምርታማ እና ዘላቂ የምግብ ሥርዓትን ለመገንባት የአየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ወሳኝ መሆኑን ነው የገለጹት።
በሳይንስ፣ በማስረጃ እና ውጤታማ በሆኑ የእውቀት ሽግግር ላይ የተመሰረቱ ፈጠራ የታከለባቸው እና የተቀናጁ ቀጣናዊ ምላሾችን ይሻሉ ብለዋል።
አውደ ጥናቱ የኢጋድ አባል አገራት የምግብ ሥርዓቶች የመቋቋም አቅም ፕሮግራም ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው፤ የቀጣናውን ተጨባጭ ሁኔታዎች በትክክል የሚያንፀባርቅ እና ወደ ተግባር ሊቀየሩ የሚችሉ ምክረ-ሃሳቦች እንዲሁም ቴክኒካዊ እውቀት ለማጎልበት ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።