ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቀጣናውን የኃይል ትስስር ይበልጥ በማጠናከር የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የቀጣናውን የኃይል ትስስር ይበልጥ በማጠናከር የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ገለጹ።

የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) የቀጣናውን የኃይል ንግድ በይፋ ለማስጀመር የሚያስችልና አባል ሀገራትን መግባባት ላይ የሚያደርስ ልዩ ስብሰባ ማካሄድ ጀምሯል።

ይህ መድረክ አባል ሀገራትን መግባባት ላይ ለማድረስና የቀጣናውን የኃይል ንግድ በይፋ ለመክፈት ያለመ ወሳኝ ምዕራፍ ነው።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል በቀጣናው አስተማማኝና ዘላቂ አቅርቦት ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ይህ የኃይል ትስስር ለኢትዮጵያ ትልቅ የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባለፈ፣ በአባል ሀገራቱ መካከል በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ ዘርፎች ጠንካራ መስተጋብር እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በአሁን ወቅት ይህንን ቀጣናዊ መስተጋብር ወደ አንድ የጋራ የአፍሪካ የኃይል ትስስር ለማሳደግ መጠነ-ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) ሊቀመንበር ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፤ የኃይል ትስስሩ ለሀገር በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት አብራርተዋል።

የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ተሰሚነትና የዲፕሎማሲ አቅም ከማሳደግ ባለፈ፤ ከኃይል ሽያጭ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ እያስቻላት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት ከኬንያ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲና ታንዛኒያ ጋር ስምምነት በመፍጠር ኃይል እያቀረበች መሆኗን ጠቁመዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለውም፤ በቀጣይም ከደቡብ ሱዳን እና ከሶማሊያ ጋር የኃይል ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም