የኢትዮጵያ የብዝኅ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራ ምርታማነትን በማሻሻል የዘርፎችን ውጤታማነት አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብዝኅ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራ ምርታማነትን በማሻሻል የዘርፎችን ውጤታማነት አሳድጓል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የተከተለችው የብዝኅ-ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራ ስኬታማ የሪፎርም ሥራዎች ምርታማነትን በማሳደግ የዘርፎችን ውጤታማነት ማሳደጉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው፣ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ መንግሥት የጀመራቸው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ተከታታይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ግብርና 7 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘንድሮ 29 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማስፋፋትና ለማዘመን ከተያዙ ቁልፍ ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪው ክፍለ-ኢኮኖሚ ዋነኛውና የትኩረት ማዕከል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከለውጡ በፊት በሀገሪቱ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ47 በመቶ በታች የነበረው የማምረት አቅም አሁን ላይ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ እንዳሉት፤ በአምስት ዓመታት የምክር ቤት ዘመን ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እመርታን አስመዝግባለች።
በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመትም በብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የተኪ ምርት አቅምን በማሳደግ በወጪ ንግድ ጭምር ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ቁርጠኝነት፣ የዜጎች ትብብርና የመሪነት ሚናም ኢትዮጵያ ላስመዘገበችው እመርታ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አንስተዋል።
በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ አዋጆች በማፅደቅ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር የህዝብ ውክልና ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች የልማት ዘርፎች ውጤታማ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ በማስቻልና የከተማ ገፅታን በመቀየር በርካታ ስኬቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባል መስፍን እርካቤ፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ጥያቄና ችግሮች ምላሽ እያገኙ ምርታማነት እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የገጠሟትን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ተቋቁማ በሁሉም ዘርፎች የተሻለ ውጤት አስመዝግባለች ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቡኔ አለም ናቸው።
የምክር ቤት አባላቶቹ እየተከናወኑ የሚገኙት ውጤታማ የልማት ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ገልጸዋል።