ቀጥታ፡

የህወሃት ጽንፈኛ አመራሮችና የጥፋት ሃይሎች በወጣቶች ላይ የሚያካሂዱት አፈሳ እኩይ ድርጊት ነው - አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ የህወሃት ጽንፈኛ አመራሮችና የጥፋት ኃይሎች ወጣቶችን ከየትምህርት፣ ከሃይማኖት እና ከመንገድ ላይ በጉልበት እየተካሄደ ያለው አፈሳ ሰብኣዊነት የጎደለው እኩይ ድርጊት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

ሴንተር ፎር ሪስፖንሲብል ኤንድ ፒስፉል ፖለቲካ (CRPP) ከትግራይ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (TBS) ጋር በመተባበር ”ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት በትግራይ፡ የብዙኃን መገናኛ እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ሚና” በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎች ተገኝተዋል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አሁን ጊዜው የትግራይን ሰላም ማዕከል አድርጎ በቁርጠኝነት መሥራት የሚያስፈልግበት ወቅት ነው ብለዋል።

በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የልማት እንቅስቃሴዎች በትግራይም መከናወን እንዳለባቸው አመልክተው፤ ሰላም ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በጥቂት አካላት በሚንቀሳቀሱ የሕወሃት ጽንፈኛ አመራሮች ምክንያት ጠንካራውና ታታሪው የትግራይ ሕዝብ በልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሳተፍ አለመቻሉ እጅግ የሚያሳዝን መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሕወሃት ጽንፈኛ አመራሮችና የጥፋት ኃይሎች የክልሉን ሕዝብ ለዳግም ጥፋትና ስቃይ ለመዳረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ሁኔታ መላው ኅብረተሰብ በጋራና በአንድ ድምፅ በመቆም ሊቀለብሰው እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

አመራሩን ሳይቀር ከሞት ያዳኑ ወጣቶች ሰላም ሊሰፍን ይገባል ብለው ባመኑበት ወቅት፤ ከየትምህርት ቤቱ፣ ከየገዳማቱ፣ ከቤተክርስቲያንና ከመስጊዱ በጉልበት እየታፈሱ ይገኛል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት የሚሰራጩ መረጃዎች በተለይም ከተለያዩ አካባቢዎች ድምፅ ለሚሆኑ ዜጎች የሚቀርቡ ዘገባዎች ጊዜውንና ሁኔታውን ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

አሁን የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ያገናዘቡና የሀገሪቱን እንዲሁም የቀጣናውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ያስገቡ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

ሴንተር ፎር ሪስፖንሲብል ኤንድ ፒስፉል ፖለቲካ ጄነራል ማናጀር ሳሙኤል አባተ እንዳሉት፤ ሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች የተሰጧቸውን መድረኮች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ወጣቶችን ወደ ሌላ የስቃይ አዙሪት የሚገፋፋ ማንኛውንም ዓይነት መልዕክት በፅኑ መቃወም እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለእርቅ፣ ለእውነት፣ ለዴሞክራሲያዊ ተሳትፎና ሕዝብን ማዕከል ላደረገ ልማት የድርሻቸውን ማበርከት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም