ማኅበሩ ተደራሽነቱን በማስፋት የሰብአዊ አገልግሎት ተግባራትን ይበልጥ ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
ማኅበሩ ተደራሽነቱን በማስፋት የሰብአዊ አገልግሎት ተግባራትን ይበልጥ ያጠናክራል
ጋምቤላ ፤ሰኔ 30/2018 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ተደራሽነቱን በማስፋት እያከናወናቸው ያሉትን የሰብአዊ አገልግሎት ስራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
በማኅበሩ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 17ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሄዷል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቅርንጫፍ ጉዳዮችና ሎካላይዜሽን ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ መሐመድ ጀማል በጉባኤው ላይ እንዳሉት፣ ማኅበሩ ተደራሽነቱን ይበልጥ በማስፋት የተጠናከረ የሰብአዊ አገልግሎት ተግባሩን ለመወጣት ትኩረት ሰጥቷል።
ማኅበሩ ካሉት ከ7 ሚሊዮን በላይ አባላቱ መዋጮ በመሰብሰብ በሚያጋጥሙ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ ቀድሞ በመድረስ ለዜጎች ሰብአዊ ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ማኅበሩ በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉት ከ800 በላይ አምቡላንሶችና ከ90 በላይ መድኃኒት ቤቶች አማካኝነት ለማኅበረሰቡ ሰብአዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም መንግሥት የሰብአዊ ድጋፎችን በራስ አቅም ለመሸፈን ለያዘው ግብ መሳካት ማኅበሩ የድርሻውን ለመወጣት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ዋና ፀሐፊው ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ ኢንጂነር ማክበዲ ኡቻን በጉባኤው ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ማህበሩ በአስቸጋሪ ወቅቶችና ፈተናዎች ወቅት ቀድሞ በመገኘት ያለ ምንም ልዩነት ለዜጎች ሰብአዊ ድጋፎችንና አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ላይ ቀድሞ በመድረስ ሲሰጥ ለቆየው በርካታ የሰብአዊ ድጋፍና አገልግሎት የክልሉ መንግሥት ምስጋናውን ይገልፃል ብለዋል።
ተወካዩ አክለውም ማኅበሩ በቀጣይም የጀመራቸውን በጎ ተግባራት በተሻለ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመው፣ ለሥራዎቹ መሳካት የክልሉ መንግሥት ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ማኅበሩ በነበረው የአንድ ቀን ጠቅላላ ጉባኤ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን የአራት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጦ፣ ውይይት ካደረገበት በኋላ አፅድቋል።
ጠቅላላ ጉባኤው በየአራት ዓመቱ በሚያካሄደው አዲስ የቦርድ አባላት ምርጫ መሠረት፣ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚመሩ ሰባት የቦርድ አባላትን በመምረጥ ጉባኤው ተጠናቋል።