ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሩሲያ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ የትብብር ምዕራፍ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታወቁ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሩሲያ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ የትብብር ምዕራፍ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፥ ሚኒስትሮቹ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ትብብር መስኮች ላይ መክረዋል።


 

በውይይቱ በዋናነት ከተነሱት ጉዳዮች መካከል የኢኮኖሚና የንግድ ትስስርን ማሳደግ አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን የቡና ኤክስፖርት ማሳደግና ከሩሲያ የሚመጣውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት ማረጋገጣቸውንም አስረድተዋል።

በዲፕሎማሲው ረገድም ኢትዮጵያ በብሪክስ (BRICS) አባልነቷ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም በአፍሪካ ህብረት መድረኮች ላይ ከሩሲያ ጋር የምታደርገውን የውጭ ፖሊሲ ቅንጅት ይበልጥ ለማጎልበት ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም