የአፍሪካ ህብረትና ሩሲያ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ትብብራቸውን ለማሳደግ ቁርጠኝነታቸውን አረጋገጡ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ህብረትና ሩሲያ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ትብብራቸውን ለማሳደግ ቁርጠኝነታቸውን አረጋገጡ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት እና ሩሲያ የጋራ ጥቅምን ማዕከል ባደረገ መልኩ፣ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ አስታወቁ።
ዓመታዊው የአፍሪካ ህብረት እና ሩሲያ የከፍተኛ ደረጃ ምክክር ዛሬ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተካሂዷል።
በምክክሩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የህብረቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ እና ልዑካን ቡድናቸው ተሳትፈዋል።
ውይይቱ በጋራ መከባበር፣ በሉዓላዊ እኩልነትና በጋራ ጥቅሞች ላይ የተገነባውን፣ እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የአፍሪካ እና የሩሲያን አጋርነት ይበልጥ ያጸና መሆኑ ተመላክቷል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን እና አጀንዳ 2063ን በተጨባጭ መደገፍ የሚያስችሉ ቁልፍ የትብብር መስኮች ላይ ምክክር ተደርጓል።
በዚህም መሠረት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ መሠረተ ልማትና ኢነርጂ ልማት ላይ ከመተባበር ባለፈ፤ በቴክኖሎጂ፣ በምግብ ዋስትና፣ በማህበረሰብ ጤና እና በኢንዱስትሪ ሽግግር ዙሪያ ያሉ ስትራቴጂካዊ አጋርነቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል።
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲሁም በሰብዓዊ ድጋፍ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ምግብ ዋስትና እና አቅም ግንባታ አስመልክቶ እያደረገች ያለውን ዘለቄታዊ ድጋፍ አድንቀዋል።
በተጨማሪም በሰላም እና ደህንነት፣ በአፍሪካ-መር የግጭት አፈታት መፍትሄዎች፣ በአፍሪካ ህብረት እና በተመድ መካከል ያለውን የሰላምና ጸጥታ ትብብር ማጠናከርን ያለመው የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ 2719 አፈፃፀምና በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ አፍሪካ ሙሉ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ሁለት ቋሚና አምስት ቋሚ ያልሆኑ መቀመጫዎች እንዲኖሯት የሚጠይቅ የአፍሪካ ኅብረት የጋራ የፖሊሲ አቋም (Ezulwini Consensus) ዙሪያም ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
የባለብዙ ወገን ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የአፍሪካን ቋሚ ውክልና ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ይበልጥ አሳታፊ እና ፍትሃዊ እንዲሆን እየተደረገ ላለው ጥረት ድጋፏን ማድረግ እንደምትቀጥል አመልክተዋል።
ላቭሮቭ ለአፍሪካን የኢኮኖሚ ዕድገት አድናቆት የቸሩ ሲሆን፣ የአህጉሪቱ የግብርና እና የማዕድን ምርቶች ላይ እሴት መጨመር አለበት በማለት ሊቀመንበሩ ላቀረቡት ጥሪም አጋርነታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ሰብዓዊ ኤጀንሲንና የአፍሪካ መድኃኒት ኤጀንሲን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረትን ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር ሩሲያ ድጋፏን እንደምታደርግ ተናግረዋል።
ሁለቱ መሪዎች የአፍሪካ ህብረት እና የሩሲያን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማሳደግ እንዲሁም በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም የሚካሄደው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ዝግጅት ስኬታማ እንዲሆን ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት መግለጻቸውን የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።