ቀጥታ፡

‎በምክር ቤት የነበራቸውን ቆይታ ያጠናቀቁ አባላት ከመንግሥት ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ለማገልገል ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነበራቸውን ቆይታ ያጠናቀቁ አባላት፣ ከመንግሥት ጋር በመሆን ኢትዮጵያን የማገልገልና ሀገርን በጋራ የማልማት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በመገኘት የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው ወቅት፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በምክር ቤቱ ከፍተኛ ሀገራዊ አገልግሎት ሲያበረክቱ ለቆዩና በሚቀጥለው የምክር ቤት ዘመን ለማይቀጥሉ የብልፅግና ፓርቲም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንዲሁም የግል ተወዳዳሪዎች በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ሕዝብና መንግሥትን በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩና የምክር ቤት የስራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የብልፅግና ፓርቲ አባላት በፓርቲና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተለያየ ደረጃ አገልግሎታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ድርጅቱና መንግሥት የላቀ ምስጋና እና ክብር ያቀርብላችኋል ሲሉም ገልጸዋል።

አባላቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በእውቀታቸውና በአቅማቸው ልክ ሀገራቸውን ማገልገላቸውንና በምክር ቤቱ ውስጥ የሕዝብን ድምፅ ማሰማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና የግል ተወዳዳሪዎችም ባለፉት አምስት ዓመታት በምክር ቤት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነው፤ በምርጫው ውጤት መሠረት በአዲሱ ምክር ቤት የማይቀጥሉ አባላት በምክር ቤት ቆይታቸው ማብቂያ ሀገራዊ አገልግሎታቸውን የሚያቆሙበት ሊሆን እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

ከምክር ቤት ውጪ ከመንግሥት ጋር ሆነው ኢትዮጵያን እንዲያገለግሉ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት እነርሱን አካቶ ኢትዮጵያን ማልማት እንደሚፈልግም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሁሉም የጋራ ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ ትብብሩ በምክር ቤት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች ሊቀጥል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በምክር ቤት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች ተባብሮ ኢትዮጵያን ማበልጸግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ አብረን እንስራ ሲሉ ጥሪ በማቅረብ አብሮ የመሥራት ጉዟቸው መቋጫ እንዳይኖረው ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም