ባለፉት አምስት ዓመታት 40 ሺህ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት አምስት ዓመታት 40 ሺህ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል
አዳማ፣ ሰኔ 30/2018 (ኢዜአ)፡- ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 40 ሺህ አዳዲስ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሞጆ-አዳማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ፕሮጀክቱ በርካታ ውስብስብ ፈተናዎችን አልፎ በተቀመጠለት ጊዜ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን አዳማ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ማዕከል እንደመሆኗ፣ ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት የተሟላ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 40 ሺህ አዳዲስ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም ከእነዚሁ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የጎዴና ቢቸና ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተዋል።
የክልሉ መንግሥት የከተሞችን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍና በዘርፉ የሚነሳውን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱረህማን ናቸው።
የክልሉ መንግስት የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ጨምሮ በገጠርና በከተሞች የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ለመመለስና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የመጠጥ ውሃ ጥያቄው በየጊዜው በጨፌው ላይ የሚነሳ መሆኑን የጠቀሱት አፈ ጉባኤዋ፣ የሞጆ-አዳማ ፕሮጀክት ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መጀመሩ የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ ከመሰረቱ የመለሰ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ከተሞች በውሃ አስተዳደርና አጠቃቀም ራሳቸውን እንዲችሉ የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች መዘርጋታቸውን ጠቅሰው፤ የአዳማ ከተማ አስተዳደር በቴክኖሎጂ የታገዘ ዲጂታል አሰራር ተግባራዊ በማድረጉ የፋይናንስ አቅም መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
ይህም በጥገና፣ በእድሳትና በማስፋፊያ ስራ ራሳቸውን እንዲችሉ ያደርጋቸዋል ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ እንደተናገሩት፣ በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 2 ሺህ 233 የውኃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በመብቃታቸው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ዛሬ የተመረቀው ፕሮጀክትም 15 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች፣ 250 ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታ እና በቀን 77 ሺህ ሜትር ኪዩብ ንጹህ ውኃ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ፣ የሞጆ-አዳማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መመረቅ የከተማዋን የዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የመለሰና ቅሬታዎችን የፈታ ነው ብለዋል።
"ፕሮጀክቱ ረጅም ጊዜን የወሰደና ብዙ ውስብስብ ችግሮችን ያለፈ ቢሆንም፣ ዛሬ ትልቁ ህልማችን እውን ሆኗል፤ የከተማዋን ህዝብ የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ለመፍታት ያስቀመጥነውን ግብም አሳክተናል" ሲሉም ገልጸዋል።
ከንቲባው አክለውም፣ ይህ ስኬት አዳማን የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ለተያዘው እቅድ ትልቅ አቅምን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።