ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ እያስገኘ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል

ጎንደር፤ሰኔ 30/2018 (ኢዜአ):- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ- ግብር እያስገኝ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማስቀጠል ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኜው ገለጹ። 

ከተማ አስተዳደሩ የክረምት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአዘዞ ክፍለ ከተማ በአባ ሳሙኤል ፓርክ  ዛሬ አስጀምሯል።


 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ቻላቸው ዳኜው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ- ግብር ባጭር ጊዜ ውስጥ ዘርፈ ብዙ እና ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ ያስቻለ ነው።

በመርሃ- ግብሩ የለሙ ተፋሰሶች አርሶ አደሩ በመስኖ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በንብ ማነብ ፣ በመኖና ሌሎች የልማት ዘርፎች በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆን የቻለበት ነው ሲሉ ገልፀዋል።

በተለይም በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት አርሶ አደሩ ዘላቂና ተጨማሪ ሃብት እንዲያፈራ መርሃ ግብሩ ሰፊ እድል ለመፍጠር እያስቻለ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በመሆኑም በዘንድሮው ዓመትም የአትክልት ፍራፍሬና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ላይ በማተኮር  የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንደሚካሔድ አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አበራ አደባ ፤በበኩላቸው በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ476 ነጥብ 5 ሔክታር  መሬት ላይ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በተካሄደው መርሃ ግብርም 758 ሺህ ዜጎችን በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

በዘንድሮ ዓመትም ባለፉት ዓመታት የተገኘውን ተጠቃሚነት ለማስፋትም 500 ሺህ የአቡካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አስገንዝበዋል።

የተተከሉ ችግኞችን የመጽደቅ ምጣኔ 95 በመቶ ለማድረስ ማህበረሰቡን ያሳተፈ የእንክብካቤና ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን አስገንዝበዋል። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለእንስሳት መኖ፣  ለንብ ማነብ፣ ለከብት ማድለብና በወተት ልማት ዘርፍ እድገት ማስመዝገብን ጨምሮ ስርአተ ምግብም እንዲሻሻል ማድረጉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም