ቀጥታ፡

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

ቡታጅራ፤ ሰኔ 30/2018 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ ቀመሪያ ረሻድ የቢሮውን የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫን በማስመልከት ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በክልሉ ገቢን  በአግባቡ በመሰብሰብ የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በተሰራው ሥራ ውጤት መገኘቱንና ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በ2018 በጀት ዓመት ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ መቻሉንም አስታውቀዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ9 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

በቀጣይም የግብር አሰባሰብ ሥራውን ለማሳካት የግብር ህጉን የማስከበርና ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች በተከታታይነት እንደሚሰሩ አንስተዋል። 

በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብር አሰባሰብ ሂደትንና ቅንጅታዊ  ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስረድተዋል።

በዚህም ክልሉ በ2019 በጀት ዓመት ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ለመሰብሰብ መታቀዱን ያነሱት ሃላፊዋ፣ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ከሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ግብሩን በታማኝነት በመክፈል ሃላፊነቱን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።  

በክልሉ የሚገኙ ከ115 ሺህ 790 በላይ የደረጃ የ "ሀ" እና "ለ" ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በወቅቱ በመክፈል ለክልሉ ልማት መጠናከር የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

የገቢ አሰባሳብ ስርዓቱን በማዘመን ቀልጣፋና ፈጣን የገቢ አሰራርን ተግባራዊ መደረጉን ያነሱት ሃላፊዋ፣ ግብር ከፋዮችም የጊዜና ጉልበት ብክነትን በሚታደጉ የቴክኖሎጂ አማራጮች ተጠቅመው ግብራቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም