ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምራ የምታጠናቅቅ ሀገር ሆናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምራ የምታጠናቅቅ ሀገር ሆናለች
አዲስ አበባ፤ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ጀምራ የምታጠናቅቅ ሀገር ሆናለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሮጀክት ግንባታ ዙሪያ ማብራሪያቸው፤ መንግስት የጀመራቸው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ተከታታይ ዕድገት ማስገኘታቸውን አስታውቀዋል።
በማሻሻያው ድጋፍ በዚህ ዓመት ብቻ በርካታ ግዙፍ ብሔራዊ ፕሮጀክቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰባት የሀገር ውስጥ ኤርፖርቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን እና ሌሎችም በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስረድተዋል።
ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት መንገድ መገንባቱ ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለረጅም ዓመታት ሳይጠናቀቁ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ በልዩ ትኩረትና ክትትል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ከዳር የማድረስና አዳዲሶቹን በሂደት የመተግበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው አቅም በፈቀደ መጠን የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች በትጋት እንደሚከናወኑ አረጋግጠዋል።