ቀጥታ፡

በክልሉ የመንግስት አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ቡታጅራ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት የተጀመሩ ተግባራት እንደሚጠናከሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የቡታጅራ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ማህበረሰቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ቅሬታዎችን መፍታት የሚያስችሉ አሰራሮችን የማጠናከር ሥራ በትኩረት ይከናወናል፡፡

በዚህም የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ ቋት በማቅረብ መስጠት የሚያስችለውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋፋት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ከማህበረሰቡ ለሚነሱ የልማት፣ የፍትሀዊ ተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በክልሉ የመንግስት አገልግሎትን ለማቀላጠፍ የሚያግዙ ማዕከላትን ከማስፋት ባለፈ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው የማዕከሉ ሥራ መጀመር ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ያጠናክራል ብለዋል።

በማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶች መሰጠቱም የማህበረሰቡን እንግልት ከማስቀረት በተጨማሪ የተጠያቂነት ስርዓትን በማስፈን ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ አህመድ እንደገለጹት፣ በከተማው ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል።

ማዕከሉ የመንግስትን አገልግሎት በማዘመን በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡

በማዕከሉ የስድስት ተቋማት 22 አገልግሎቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚደረጉም ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ የክልሉ፣ የምስራቅ ጉራጌ ዞንና የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም