ኢትዮጵያ በአለም ሶስተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር ሆናለች-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአለም ሶስተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር ሆናለች-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ለቡና ልማት የተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያን በአለም ሶስተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር እንድትሆን ማስቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው፥ ሀገራዊ የሪፎርም ስራው ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ስኬቶች ከፍተኛ አስተዋጽዎ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በዚህም በዘንድሮው አመት የኢትዮጵያ ከሸቀጦች ኤክስፖርት 11 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ገልጸው፥ከቡና ኤክስፖርት ብቻ በአመቱ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የኮፊ አረቢካ መገኛ እንደመሆኗ በየትኛውም ዘመን ቡና ወደ ውጭ ስትልክ ቆይታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥በእነዚህ አመታት ግን ይህ ነው የሚባል ገቢ ማግኘት አልቻለኝም።
በዚህም ሀገሪቱ ባለፉት 17 አመታት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ያገኘችው ገቢ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት ለቡና ልማት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ግን በዘንድሮው አመት ብቻ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማሳካት መቻሉን ጠቁመዋል።
አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለቡና ኤክስፖርት እድገት ስኬት አስተዋጽዎ ማበርከቱን ገልጸው፤ በቡና ልማት ላይ የመጣውን ለውጥ በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አክለውም፥ቡናን ካልተከልን፤ካልተንከባከብን፤ካልለቀምን፤ ካላጠብን፤ካላሸግን እና ካላጓጓዝን ይህ ውጤት ሊመጣ አይችልም ብለዋል።
የኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታ ከመቻል አልፈን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የመጣው ለውጥ የሀገራዊ የሪፎርሙ ስኬት መገለጫም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቡና ልማት እና ኤክስፖርት ላይ ያሳየችው እድገት በአሁኑ ሰዓት ከብራዚል እና ኮሎምቢያ ቀጥላ በአለም 3ተኛ ደረጃ እንድትይዝ አድርጓታል ሲሉ ተናግረዋል።