የኢትዮጵያን የምርታማነት አቅም ይበልጥ በማሳደግ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በትኩረት ይሠራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የምርታማነት አቅም ይበልጥ በማሳደግ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በትኩረት ይሠራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የምርታማነት አቅም ይበልጥ በማሳደግ እና የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ከተወሰዱ ቀዳሚ እርምጃዎች መካከል የሸማቾችን አማራጭ ማሳደግ አንዱ ሲሆን፣ በዚህም የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ተደራሽነት ከ2000 በላይ ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።
የኑሮ ውድነቱን ጫና ለማቅለል መንግሥት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድጎማ እያደረገ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም በነዳጅ ዘርፍ ላይ ይደረግ የነበረው ድጎማ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን አስታውቀዋል።
ቀድሞ የነበረው የነዳጅ ድጎማ በወር 16 ቢሊዮን ብር እንደነበር ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት 20 ቢሊዮን ብር በመጨመር የድጎማ መጠኑን በወር ወደ 36 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።
ይህ የሕዝቡን የመግዛት አቅም ለማሳደግ የተመደበ ትልቅ ሀገራዊ አቅም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በየደረጃውና በልፋታቸው ልክ ተጠቃሚ ማድረግ አለበትም ነው ያሉት።