ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የሕክምና አገልግሎት የመስጠት አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የሕክምና አገልግሎት የመስጠት አቅም ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጤናው ዘርፍ  በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ማምረት አቅም ከነበረበት 4 በመቶ አሁን ላይ ወደ 44 በመቶ ማደግ እንደቻለ ገልጸዋል።

ለአጠቃላይ መድኃኒት ግዢ 70 ቢሊዮን ብር፣ ለሕክምና መሣሪያዎች ግዢ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ጤናውን ዘርፍ አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማስፋት የተደረገ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ወራት በርካታ ሆስፒታሎችን ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውና በሚቀጥሉት ወራት የሚመረቁ ሌሎች ተቋማት መኖራቸውም የጤናውን ዘርፍ እመርታዊ ውጤት እንደሚያሳይ አንስተዋል።

ለአብነትም ለግንባታ ሂደት ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን የአልጋ አቅም በአንድ ሺህ ያሳደገው አዲሱ ሕንፃ ተምሳሌት መሆኑን አስረድተዋል።

በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ተደርገውእየተሰሩ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በቀጣይም በውጭ ሀገራት የሚታዩ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎችን በኢትዮጵያ መገንባት መሆኑም አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል የወባ በሽታን ለመቀነስ በተደረገው የተቀናጀ ጥረት 14 ሚሊዮን አጎበር የተሰራጨ ሲሆን፣ በ3 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶች ላይ ደግሞ የጸረ-ወባ ኬሚካል የእርጭት መርሃ ግብር መካሄዱን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም፣ ቀደም ሲል የክትባት ተደራሽነት ባልነበረባቸው 58 ወረዳዎች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ክትባት መስጠት መቻሉን አስታውቀዋል። 

መንግስት የጤናው ዘርፍ የህክምና አገልግሎት የመስጠት አቅሙን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ እስፈላጊ ልማቶችን ለማስፋፋት የሰራቸው ተግባራት አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም