ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ቅንጣት ታክል ስጋት የሚሆን አንዳች ኃይል የለም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ቅንጣት ታክል ስጋት የሚሆን አንዳች ኃይል የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዲፕሎማሲው ዘርፍና በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው፤ ኢትዮጵያ በመቋቋም፣ በመጠቀምና በመግራት የዲፕሎማሲ መርሆች አማካኝነት ብሔራዊ ጥቅሟን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅ አቅም መገንባቷን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጠላቶች ከሀገሪቱ ፍላጎቶችና ብሔራዊ ጥቅሞች በተጻራሪ የሆኑ፣ በሦስት 'መ'ዎች ላይ የተመሰረቱ ስሁት መርሆችንና ስሌቶችን እየተከተሉ መሆኑን አስረድተዋል።

መካድ፦ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ያላት፣ አልገዛም የሚል ሕዝብ ያላት፣ ሊገዟት ብዙ ጊዜ ሞክረው ተሸንፈው የተመለሱባት ሀገር መሆኗንና ሀገሪቱን ማንበርከክ ቀላል አለመሆኑን ታሪክ ቢያውቅም፤ ጠላቶቿ ግን ይህንን እውነት ይክዳሉ ብለዋል።

መርሳት፦ ጠላቶች በዚህ ስሁት መንገዳቸው ይህቺ ሀገር ስትራቴጂካዊ ጥልቀት ያላት፣ የሰብዓዊ ኃይል ትርፍ ያላትና የወጣቶች ሀገር መሆኗን፣ እንዲሁም በክፉ ጊዜ ራሷን መከላከል እንደምትችል ይረሳሉ ነው ያሉት።

የሀገሪቱ አቀማመጥና ተቋማዊ ልምምዱ ቀላል አለመሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጠላቶች ይህንን በመርሳት ስሁት ስሌት ውስጥ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።

በዚህም ምክንያት ስለ እኛ ሲያስቡ ድህነታችንን እንጂ እምቢ ባይነታችንን ማስታወስ እንደማይፈልጉና አንዳንዴም ማራከስ እንደሚሹ አንስተዋል።

ምኞት፦ የዚህ ጊዜ ያለፈበት ስልትና ምኞት እስረኛ መሆንም ሌላኛው የጠላቶች ስሁት ስሌት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ማጠቃለያ፤ የትኛውም የሀገር ውስጥ ባንዳና የውጭ ጠላት ቢተባበር እንኳ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ቅንጣት ታክል ስጋት እንደሌለ በአስተማማኝ ሁኔታ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም