የመንግሥት ዋና ፍላጎት ሁልጊዜም ሰላምና ልማት ብቻ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት ዋና ፍላጎት ሁልጊዜም ሰላምና ልማት ብቻ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከየትኛውም ዓይነት ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስጠብቅና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ የሚያስችል በቂ እና አስተማማኝ የጸጥታ ኃይል መገንባቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው፣ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ መንግሥት ሁልጊዜም ቢሆን ለሰላም ያለው በር ክፍት መሆኑን ገልጸው፣ አሁንም ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ከምንጊዜውም በላይ በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ፣ ሀገሪቱን ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አስተማማኝ ቁመና መገንባቱን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ ጽንፈኛ ኃይሎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ሀገሪቱን ለማተራመስ ቢሞክሩም ፍላጎታቸው እንደማይሳካ ገልጸዋል።
ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብና የውጊያ ስልት የሚከተሉ እነዚህ ኃይሎች የሰላምን መንገድ ቢመርጡ እንደሚሻላቸው አስታውሰው፤ ከዚያ አልፈው ጥፋት ለማድረስ የሚመጡ ከሆነ ግን አስተማሪ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠንቅቀዋል።
በትግራይ ክልል ያሉ አንዳንድ ኃይሎች ዳግም ጦርነት የመቀስቀስ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ የማያዋጣ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማሳሰብ የመንግሥት ዋና ፍላጎት ሰላምና ልማት ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ እኔ ካልመራሁ አይሆንም በሚል ግጭት ለመቀስቀስ የሚደረግ አካሄድ ለማንም አይጠቅምም፤ በአሁኑ ወቅት ለሀገሪቱ ወሳኙ ነገር ሰላም ነው ብለዋል።