ቀጥታ፡

የሀገር ውስጥ መድኃኒት የማምረት አቅም ከነበረበት 4 በመቶ ወደ 44 በመቶ ማሳደግ ተችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2018(ኢዜአ)፦ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ማምረት አቅማችንን ከነበረበት 4 በመቶ ወደ 44 በመቶ ማሳደግ ችለናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)‎‎የጤና ጉዳዮችን በሚመለከት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ማምረት አቅማችንን ከነበረበት 4 በመቶ ወደ 44 በመቶ ማሳደግ ችለናል ብለዋል።

ለአጠቃላይ መድኃኒት ግዢ 70 ቢሊዮን ብር፣ ለሕክምና መሣሪያዎች ግዢ ደግሞ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርገናል ሲሉም ተናግረዋል።

ባለፉት ወራት በርካታ ሆስፒታሎች ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቁመው በሚቀጥሉት ወራት የሚመረቁ ሌሎች ተቋማት ይኖራሉ ሲሉም አስታውቀዋል።

ለግንባታ ሂደት ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልን የአልጋ አቅም በአንድ ሺህ ያሳደገው አዲሱ ሕንፃ ተጠቃሽ መሆኑንም አክለዋል።

በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ተደርገው የተሰሩ መሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል።

ቀጣዩ ትኩረታችን በውጭ ሀገራት የምናያቸውን ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎችን በሀገራችን መገንባት ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ የወባ በሽታን ለመቀነስ በተደረገው የተቀናጀ ጥረት 14 ሚሊዮን አጎበር መሰራጨቱን አንስተው በ3 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶች ላይ ደግሞ የጸረ-ወባ ኬሚካል ተረጭቷል ነው ያሉት።

በተጨማሪም፣ ቀደም ሲል የክትባት ተደራሽነት ባልነበረባቸው 58 ወረዳዎች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ክትባት መስጠት ተችሏል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምላሽ እና ማብራሪያቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም